የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በያዝነው የክረምት ወራት ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን የበጎ አድራጎት ስራዎችን ለመስራት አቅጣጫ ማስቀመጡን አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ( አዲስ ቻምበር) በሀገሪቱ በተለይም በከተማችን እየሰፋ የመጣውን ድህነት፣ የኢኮኖሚ ችግሮችና የዋጋ መናር በዜጎች ላይ እያስከተለ ያለውን ከፍተኛ የኑሮ ውድነት በመገንዘብ ምክር ቤቱ የማህበራዊ ሃላፊነት ተግባሩን ለመወጣት የሚያስችለውን አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ በከተማው የተለያዩ አከባቢዎች ነዋሪ ለሆኑ ቁጥራቸው ከ3000 እስከ 5000 ለሚደርሱ ችግረኛ ቤተሰቦችና ግለሰቦች በያዝነው የክረምት ወራት የምግብ ፕሮግራምና የምግብ ቁሳቁሶችን ለማከፋፈል በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡
ይህ ከአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሚሰራው የበጎ አድራጎትና የልማት ስራ ማእድ ማጋራት፤ የአቅመ ደካማ ዜጎች መኖርያ ቤቶችን ማደስና የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ይገኙበታል፡፡ ከእያንዳንዱ ስኬት ጀርባ እኛ የሚለው ሀሳብ አለና እኛ በጥምረትና በመተሳሰብ በመስራት አዲስ ቻምበር የጀመረውን በጎ ተግባር ይምጡና ይቀላቀሉ የሚል መልእክትም አስተላልፏል ምክር ቤቱ፡፡ ለዜጎች አለኝታ በመሆን የተሻለ ሀገርና ማህበረሰብ እንዲፈጠር ሁሉም ባለ ድርሻ አካል ማኅበራዊና ሞራላዊ ግዴታውን እንዲወጣ ጭምር ምክር ቤቱ መልእክቱን አስተላልፏል፡፡ በዚህ ተግባር ለመካፈል እና በአይነትም ሆነ በቁስ ድጋፍ ለማድረግ የሚሹ ግለሰቦችና ተቋማት በድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት በመገኘት የፕሮጀክቱን ዝርዝር አለማ ማግነት እንደሚችሉ ምክር ቤቱ መልእክቱን አስተላልፏል፡፡