አዲስ ቻምበር ‘የታክስ ስርአት አተገባበር በግሉ ዘርፍ ላይ ያለው ተጽእኖ በሚል የፓናል ውይይት በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የታክስ አሠራር እና አተገባበር ቀልጣፋና ለንግድ አሰራር አስቻይ እንዲሆን አሁን ያለው የታክስ ፖሊሲና ሕግ፤ መመሪያ ወደፊት ከሚታሰበው የግል ዘርፉ ሚና አኳያ መቃኘት እንደሚኖርበት ተገልጿል::
(ሰኔ 6፤ 2016 ፤ አዲስ ቻምበር )
አዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ‘የታክስ ስርአት አተገባበር በግሉ ዘርፍ ላይ ያለው ተጽእኖ በሚል የፓናል ውይይት በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው፡፡
የፓናል ውይይቱን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የከፈቱት የአዲስ ቻምበር ዋና ፀሃፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም እንደተናገሩት ምክር ቤቱ በግሉ ዘርፍና በመንግሥት መካከል እንደ አገናኝ ድልድይ ሆኖ ከሚያከናውናቸው ሥራዎች መካከል ለግሉ ዘርፍ አመቺ የሆኑ ህጎችና ፖሊሲዎች እንዲወጡለትና ተግባራዊ እንዲሆኑለት እንዲሁም አፈጻጻማቸው የተሳለጠ እንዲሆን ጥረት ማድረግ ነው ብለዋል፡፡
ምክር ቤቱ ምቹ የንግድ ከባቢ ሁኔታ ፤አመቺ አሰራሮችና ፖሊሲዎች እውን እንዲሆኑ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
የግሉ ዘርፍ በግንባር ቀደምትነት ካስቀመጣቸው ለቢዝነስ ፈታኝ ከሆኑ ጉዳዮች መካካል የታክስ ጉዳይ ከፍተኛውን ድርሻ መያዙን በመድረኩ ላይ ጠቁመዋል::
በመድረኩ ላይ የተገኙትና የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ እንደተናገሩት የግሉ ዘርፍ እድገት ማነቆ ተብለው ከተዘረዘሩት መካከል ግብር ዋነኛው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተለይ በአዲስ አበባ ውስጥ በተለያዩ የንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩና በተለያየ ደረጃ ያሉ ግብር ከፋይ አባሎቻችን በግብር እና በታክስ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያቀርቡትን ቅሬታ ም/ቤቱ ተቀብሎ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ችግሮች እንዲፈቱ እንዲህ አይነት የአድቮኬሲና የምክክር መድረክ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
እንዲህ አይነቱ መርሃግብር የግብር ጉዳዮች ላይ መተማመንን በማስፈን እና ችግሮችም ካሉ በመቅረፍ መንግሥት መሰብሰብ የሚጠበቅበትን ገቢ እንዲሰበሰብ ያደርጋል ብለዋል፡፡
የታክስ አስተዳደሩ የታክስ አሰባሰብ ቅልጥፍና ችግር፤ የታክስ ፖሊሲ ክፍተት፤ የህብረተሰቡ ግብርን የመክፈል ባህል አናሳ መሆን፤የመረጃ አሰጣጥ ችግር፤የሰው ሀይል እና የቴክኖሎጂ ክፍተቶችን በተግዳሮትነት አንስተዋል፡፡
በፓናል ውይይቱ የተለያዩ የመነሻ ጽሁፎች የሚቀርቡ ሲሆን ከአቅራቢዎቹ መካከል ኮማንደር አህመድ መሀመድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ምክትል ቢሮ ኃላፊ፤ አቶ ተስፋዬ መርጊያ በገቢዎች ሚኒስቴር የታክስና ጉምሩክ ስልጠና ማእከል ሃላፊ፤ አቶ ያየህይራድ አባተ የጄቲአይ ኩባንያ ኮርፖሬት ጉዳዮችና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር፤ ዶ/ር አስቻለው ተሻገር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት ረዳት ፕሮፌሰር እንዲሁም አቶ አዲሴ ሽፈራው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር ይገኙበታል፡፡
በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ የታክስ አሠራር እና አተገባበር ቀልጣፋና ለንግድ አሰራር አስቻይ እንዲሆን አሁን ያለው የታክስ ፖሊሲና ሕግ፤ መመሪያ ወደፊት ከሚታሰበው የግል ዘርፉ ሚና አኳያ መቃኘት እንደሚኖርበት ተገልጿል፡፡
ይህ በአዲስ ቻምበር የተዘጋጀው የፓናል የውይይት መድረክ ዋና አላማ በግብር ዙርያ የንግዱ ማህበረሰብ የሚጋጥማቸውን ተግዳሮት በሚመለከታቸው አካላት ምላሽ እንዲያገኝ ግፊት ማድረግ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት በግብር መልክ የምትሰበስበው ታከስ ከሰሀራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ጋር ሲነጻጻር አናሳ መሆኑም ተመልክቷል፡፡
በግብር መልክ የሚሰበሰብ የሀገር ውስጥ ገቢ በብሔራዊ ኢኮኖሚ ውስጥ ገንቢ ሚና ካላቸው እንቅስቃሴዎች አንዱና ዋነኛው መሆኑ የተገለጻሲሆን ጠንካራና ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚ ለመገንባትና የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታን ለማስፈን የተረጋጋና ጤናማ የሆነ የግብር ስርአት መኖር ወሣኝነት አለው ተብሏል፡፡