አዲስ ቻምበር ‘‘ለዲጂታል አገልግሎት ሰጪዎች የፋይናንስ ተደራሽነትን ማሳደግ በሚል የመንግስትና ግል ዘርፍ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ አካሂዷል ፡፡

(ግንቦት 29፤ 2016 ፤ አዲስ ቻምበር ) አዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከአለም አቀፉ የግል ኢንተርፕራይዝ ማእከል ጋር በመተባበር ‘‘ለዲጂታል አገልግሎት ሰጪዎች የፋይናንስ ተደራሽነትን ማሳደግ በሚል የመንግስትና ግል ዘርፍ የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡
የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የአዲስ ቻምበር ዋና ፀሃፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም እንደተናገሩት ምክር ቤቱ በግሉ ዘርፍና በመንግሥት መካከል እንደ አገናኝ ድልድይ ሆኖ ከሚያከናውናቸው ሥራዎች መካከል ለግሉ ዘርፍ አመቺ የሆኑ ህጎችና ፖሊሲዎች እንዲወጡለትና ተግባራዊ እንዲሆኑለት ጥረት ማድረግ ነው ብለዋል፡፡
ምክር ቤቱ ምቹ የንግድ ከባቢ ሁኔታ ፤አመቺ አሰራሮችና ፖሊሲዎች እውን እንዲሆኑ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
የግሉ ዘርፍ በግንባር ቀደምትነት ካስቀመጣቸው ለቢዝነስ ፈታኝ ከሆኑ ጉዳዮች መካካል የብድር አቅርቦት አለመኖር ከፍተኛውን ድርሻ መያዙን በመድረኩ ላይ ጠቁመዋል::
ንግድ ምክር ቤቱም ራሱን በዘመናዊና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዞ ለአባላቱና ለግሉ ዘርፍ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን በመድረኩ ላይ ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙትና የቁልፍ ንግግር ያደረጉት የአለም አቀፉ የግል ዘርፍ ኢንተርፕራይዝ ማእከል የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር አቶ ሀይለመለኮት አስፋው እንደተናገሩት የግሉ ዘርፍ እድገት ማነቆ ተብለው ከተዘረዘሩት መካከል ከመሬት አቅራቦትና ከግብር በመቀጠል የብድር አቅራቦት ዋነኛው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ይህም የግሉ ዘርፍ አዳዲስ ምርት ለማምረትና ተወዳዳሪ እንዳይሆን ተግዳሮት መሆኑን አስረድተዋል ፡፡
በምክክር መድረኩ የተለያዩ ጽሁፎች የሚቀርቡ ሲሆን ከአቅራቢዎቹ መካከል በኢፌዲሪ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ካሊድ አህመድ፤ የአሸዋ ቴክኖሎጂ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዳንኤል በቀለ እና የቴክኖቢዚያ ኢንዱስትሪያል ዴቨሎፕመንት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ለሚ ቱጆ ይገኙበታል፡፡
ይህ በአዲስ ቻምበር የተዘጋጀው የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የጋራ የውይይት መድረክ ዋና አላማ በፋይናነስ አቅርቦት ዙርያ የዲጂታል አገልግሎት ሰጪዎች የሚጋጥማቸውን ተግዳሮት በሚመለከታቸው አካላት ምላሽ እንዲያገኝ ግፊት ማድረግ ነው፡፡