አራተኛው ዙር የስራ አስፈጻሚዎች መድረክ በባንኪንግ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ልምድ ያካበቱትን አቶ በቃሉ ዘለቀን እንግዳ በማድረግ ተካሄደ

(ሰኔ 26 2016 አ.ም) በአዲስ ቻምበርና በሳክ የስልጠና እና አማካሪ ድርጅት በትብብር የሚሰናዳው የስራ አስፈጻሚዎች መድረክ በተሳካ ሁኔታ በአዲስ አበባ ኢንተር ላግዥሪ ሆቴል ተካሂዷል፡፡
ሁለቱ ተቋማት የሚያዘጋጁት ይህ ወሳኝ መድረክ ለአራተኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን በዚህኛው ዙር ደግሞ በባንኪንግ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ ልምድና ተሞክሮ ያካበቱት ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ለበርካታ አመታት በፕረዚደንትነት ያገለገሉትን አቶ በቃሉ ዘለቀን በእንግድነት አቅርቧል፡፡
አቶ በቃሉ ዘለቀ ከ25 አመታት በላይ ከጀማሪ የባንክ ባለሙያ እስከ ፕረዚደንት ድረስ በማገልገል ለባንኪንግ ኢንዱስትሪው ማደግ የበኩላቸውን አስተዋጾ አድርገዋል፡፡
አቶ በቃሉ በአሁኑ ወቅት የአቢሲኒያ ባንክን በፕዚደንትነት እያገለገሉ ሲሆን በርከት ባሉ ተቋማት የቦርድ አባል በመሆን ሰርተዋል፡፡ ከነዚሀም መካከል የኢትዮጵያ ምርት ገበያ፤ኢትዮ ቴሌኮም፤ የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
Leadership in Influence በሚል መሪ ቃል የተካሄደው የስራ አስፈጻሚዎች መድረክ ላይ የካበተ ልምዳቸውን ያካፈሉት አቶ በቃሉ አንድ መሪ ስኬታማ ሊሆን የሚችለው ግልጽ የሆነ ራእይና ግብ ሲኖረው እንዲሁም ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ስትራቴጂ መንደፍ እንዲሁም ብቃት ያለው የሰው ኀይል መመደብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ አንድ መሪ ተቋምን ዘላቂ ለማድረግ ከፈለገ ከባለ ድርሻ አካላትና አጋሮች ጋር ያለውን ግንኙነት ላይ መስራት እንደሚገባ፤ ወደፊት ለሚያጋጥሙ መልካም እድሎችን እና ተግዳሮቶችን ከወዲሁ ማሰብ፤ ከስህተቶች መማር፤ ጽኑ መሆን፤ እራስን የመምራት ክህሎት ማዳበር፤ በየጊዜው ራስን በእውቀት መገንባት አንድን መሪ ስኬታማ እንደሚያደርገው የረጅም ጊዜ ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡
በዶ/ር አደራ አብደላ አወያይነት የተካሄደው አራተኛው ዙር የስራ አስፈጻሚዎች መድረክ በርካቶች የተሳተፉበት ሲሆን እንዲህ አይነት መድረኮች ሀገር በቀል የአመራር እውቆቶች ተተኪ ወጣት መሪዎች ልምድና እውቀትን የሚቀስሙበት እንዲሁም ዘላቂ የሆኑ ተቋማትን ለመገንባት የሚያስችል ጠቃሚ መድረክ ነው ያሉት ደግሞ አቶ ዘካርያስ አሰፋ የንግድ ምክር ቤቱ ምክትል ዋና ጸሀፊ ናቸው፡፡
በዚህ የስራ አስፈጻሚዎች መድረክ ላይ በመገኘት የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የምክር ቤቱ ፕረዚደንት መሰንበት ሽንቁጤ አቶ በቃሉ ዘለቀ በኢትዮጵያ የባንኪንግ ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ ያበረከቱት አስተዋጾ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አክለው እንዳሉት አቶ በቃሉ የባንክ ባለሙያዎች አቅም እንዲገነባ የነበራቸው ሚና ጉልህ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ በአዲስ ቻምበር አነሳሽነት የተጀመሩት የልምድ ልውውጥ መድረኮች በአሁኑ ወቅት የሚስተዋሉ የአመራር ክፍተቶችን ለመሙላት እና ችግሮችን ለመቅረፍ ወሳኝ ሚና አላቸው ብለዋል ፕረዚደንቷ፡፡