" ባለፉት በርካታ አስርት አመታት ሀገራችን በሯን ለውጭ የፋይናንስ ተቋማት ዝግ ማድረጓ ይታወቃል።

በእርግጥ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የፋይናንስ ዘርፉ በተለይም የባንክ ኢንዱስትሪው ለውጭ መከፈቱ አይቀሬ እንደሆነ ለሁላችንም ግልጽ እየሆነ መጥቷል፡፡
እኛም እንደ ንግድ ምክር ቤት የውጪ ባንኮች በሀገራችን የባንክ ዘርፍ ቢሳተፉ ከሚኖር ተግዳሮት ጎን ለጎን የሚገኙ እድሎችም እንዳሉ እንረዳለን፡፡
በተለይ ‹‹የግል ባንኮች ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?፣ የሚኖረው የውድድር አውድ እስከምን ድረስ ነው? የሚለው ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ መንግሥት ይህንን ዕርምጃ ዕውን ማድረጉ ምን ጥቅም ያስገኛል? ምንስ ያሳጣል? የሚለው የአባሎቻችንም ሆነ የንግድ ምክርቤታችን ጥያቄ ይሆናል፡፡
በእርግጥ የውጭ ባንኮች በሀገራችን መግባታቸው ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጥርጥር ባይኖርም አገባባቸው ግን የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን ታሳቢ ያደረገ መሆን እንዳለበት ሁሉንም ያስማማል፡፡
ይህም አጠቃላይ የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን ከማሳደግና ለአገር ከሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንፃር ታይቶ የሚወሰድ ዕርምጃ ይሆናል ብለንም እንገምታለን፡፡
የውጭ ባንኮች በሀገራችን የባንክ ዘርፍ መግባታቸው እርግጥ ከሆነ ‹‹አገባባቸው እንዴት ይሁን?›› የሚለው ጉዳይ የውይይታችን አንዱ አካል ይሆናል ፡፡ ለማንኛውም ራስን ማደርጀትና ጥሩ ተወዳዳሪ ሆኖ መቅረብ፣ መትጋት፣ ቴክኖሎጂ ላይ ኢንቨስት ማድረግ፣ በሁሉም ረገድ ራስን ማደርጀትና ለውድድሩ ብቁ ማድረግ ለነገ የሚባል ባይሆን ይመረጣል”::
የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የውጪ ባንኮች በሀገራችን የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ እንዲሰሩ መፈቀዱ ያለው እድልና ተግዳሮት በሚል የፓናል ውይይትን ለመክፈት ያደርጉት ንግግር