መንግስት በውጭ ምንዛሬ ሥርዓቱ ላይ በጥናት ላይ የተመሰረተና ቀስ በቀስ ገቢራዊ የሚደረግ ስልት እንዲከተል ተጠየቀ

የመፍትሄ ሃሳቡን ያቀረቡት በጡረታ ላይ ያሉትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የቀድሞ የባንኪንግና የውጭ ምንዛሬ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሰይፈ ደስታ ናቸው፡፡
አቶ ሰይፈ፣ በባንኩ ለበርካታ አመታት ከማገልገላቸው በተጨማሪም ከውጭ ምንዛሬና ፋይናንስ ጋር የተያያዙ በርካታ ትምህርቶችን አጥንተዋል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን ላይ ቁጥጥር የሚደረግበትና በተወሰነ ደረጃም ነፃ የሆነ የውጭ ምንዛሬ ሥርዓት እንዳላት የሚናገሩት ባለሙያው፣ የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዓርብ መጋቢት 30 ባዘጋጀውና የውጭ ምንዛሬ ገበያን ስለመክፈትና የተገኙ ልምዶች ላይ ባተኮረው የውይይት መድረክ ላይ ባቀረቡት ጥናትና ባነሱት ሃሳብ እንደተናገሩት መንግስት የውጭ ምንዛሬን በተመለከተ ማድረግ ያለበት የሁኔታዎችን ተለዋዋጭነት ከግምት ውስጥ ያስገባ፣ ቀስ በቀስና በጥናት ላይ የተመሰረተ መንገድን ገቢራዊ ማድረግ ነው፡፡
ብሔራዊ ባንክ በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የውጭ ምንዛሬን ለማግኘት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዘርፎችን የሚለይ መመሪያ ማውጣቱ ይታወቃል፡፡ እንደአቶ ሰይፈ ማብራሪያ ከሆነ የውጭ ምንዛሬ እጥረት መኖሩ ወደ ሬሽን ሥርዓት እንዲገባ ገፊ ምክንያት ሆኗል፡፡
ከሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘም ሩሲያ የአውሮፓ አገራት የነዳጅ ምርቷን ሲገዙ በራሷ ገንዘብ ሩብል እንዲከፍሉ ያስተላላፈችው ውሳኔ በኢትዮጵያ ላይስ ተፅዕኖ ይፈጥራል ወይ? የሚል ጥያቄ ከተወያዮች የቀረበላቸው አቶ ደስታ፣ ውሳኔው አውሮፓ ውስጥ ተፅዕኖ ቢፈጥርምና በሩሲያ የስቶክ ገበያ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ሩብልን ተቀባይነት ከፍ ቢያደርገውም፣ በኢትዮጵያ ላይ የሚፈጥረው ተፅእኖ አይኖርም የሚል ምላሽን ሰጥተዋል፡፡
ሌላው ለውጭ ምንዛሬ እጥረት እንደምክንያትነት የሚጠቀሰው ከውጭ የሚገቡ ምርቶች መብዛት ነው፡፡
አቶ ደስታ ጉዳዩን በምሳሌ ሲያስረዱም ከኢትዮጵያ በተሻለ የምጣኔ ሃብት አቅም ላይ በደረሱት እንደህንድ ባሉ አገራት እንኳን የውጭ አገራት ቅንጡ ተሽከርካሪዎች አይነዱም፤ ይልቁንም በራሳቸው አገር የሚመረቱትን እንደታታ የመሳሰሉ ተሽከርካሪዎችን ይጠቀማሉ፤ በኢትዮጵያ ግን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገቡ እንደቶዮታ ቪ8 ያሉ ተሽከርካሪዎችን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲፈጠር ስለማድረጉም ይሞግታሉ፡፡
ኢትዮጵያ በተለይ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በከፍተኛ ደረጃ የመቀነስና በአገር ውስጥ ምርቶች የመተካት ስልትን በፍጥነት መተግበር እንዳለባትም ባለሙያው እንደመፍትሄ ሃሳብነት ያስቀመጡት ጉዳይ ነው፡፡
በቴሌግራም ፡- https://t.me/ETIradioshow
ቤተሰብ ይሁኑን እናመሰግናለን