የግልግል ዳኝነት መሰረታዊ መርሆች ላይ ስልጠና ተሰጠ

(አዲስ ቻምበር ሰኔ 21 2018 አ.ም) ስልጠናው በንግድ ዙሪያ ለሚነሱ  ክርክሮች ግልግል ዳኝነት ላይ ለሚሳተፉ ጠበቆች አቅምን ለመገንባት የተዘጋጀ ሲሆን በግልግል ዳኝነት  አተገባበር ሂደት ውስጥ ባሉ ቁልፍ ጉዳዮች  ላይ ያተኮረ ነበር።

አዴልሻው ጎዳርድ (Addelshaw Goddard) ከተባለው እና በእንግሊዝ ከሚገኘው የንግድ ህግ አገልግሎት ሰጪ  ኩባንያ የመጡት ማርክ ሞሊኒየ እና ኒክ አሽክሮፍት የተባሉ ባለሙያዎች  የንግድ ስምምነቶች ዝግጅት ፤ስትራቴጂካዊ የቢዝነስ የአጋርነት ሰነዶች አዘገጃጀት ፣ በስምምነት ረቂቅ መካከል ስላለባቸው ዝርዝር ግዴታዎች፣ የጊዜ ገደቦች እና የፕሮጀክት ጊዜ ሰሌዳዎችን የመሳሰሉ ዘመናዊ የንግድ ስምምነቶችን የማካሄድ ስልቶችን አጋርተዋል። በሰዎች ግንኙነት ውስጥ ክርክር ተፈጥሯዊ ቢሆንም፣ የኩባንያ ጠበቆች ግን  አስቀድመው ሊከሰቱ የሚችሉ ሥጋቶችን መለየት አለባቸው፡፡ ተጨማሪ ኪሣራ  ሊያስከትሉ የሚችሉ ክርክሮችን በጥንቃቄ ማስወገድ እንዳለባቸው ተገልጿል።

አሰልጣኞቹ በኩባንያዎች መካከል የሚደረጉ የውል ድርድሮችን በሚያዘጋጁበት ወቅት ሊከተሉ ሰለሚገባቸው መርሆች ግንዛቤ አጋርተዋል። የንግድ ጠበቆች/አማካሪዎች ከክፍያ እና ከዋጋ ውሳኔ ጋር ለተያያዙ ድንጋጌዎች፣ ኃላፊነቶችን ለመወሰን፣ ሊከሰቱ የሚችሉ ከፍተኛ አደጋዎችን ለመለየት እንዲሁም ለባለቤትነት መብት (intellectual property) እና ውልን የማቋረጥ መብቶች ላይ ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል።

ተሳታፊዎችም በሥራ ላይ ካጋጠሟቸው እውነታዎች  በመነሳት በርካታ አስተያየቶችን የሰነዘሩ ሲሆን፣  በተለይ ከብድር  ሰነድ (Letter of Credit) አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው  የፋይናንስ መመሪያዎች ላይ ማሻሻያ መደረግ እንዳለበት ጠቁመዋል። የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት (አዲስ ቻምበር) የግልግል ዳኝነት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ወልደገብርኤል  ምክር ቤቱ የንግድ ክርክሮችን በግልግል ዳኝነት ለመፍታት የ80 ዓመታት የተከማቸ ልምድ አለው ብለዋል።

አገልግሎቱም ክርክር ያለባቸው ኩባንያዎች ጉዳያቸውን ከመደበኛው የፍርድ ቤት ሥርዓት በበለጠ አመቺ በሆነ መንገድ እንዲፈቱ ሲረዳ ቆይቷል ብለዋል። ስልጠናው በአዲስ ቻምበር፣ በዳዲሞስ ኤልኤልፒ እና በአዴልሻው ጎዳርድ በጋራ መዘጋጀቱን ለመረዳት ተችሏል፡፡

አዲስ ቻምበር የግሉ ዘርፍ አገልጋይ