የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በንግዱ ማህበረሰብ የተነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ከመጪው ሀምሌ ወር 2017ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተግባር ለማሸጋገር ባቀዳቸው አዳዲስ አሰራሮች ዙሪያ ከአዲስ ቻምበር አመራሮች ጋር ውይይት ተካሄደ

በውይይት መድረኩ የቢሮው ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ ቢሮው ከመጪው የግብር ማሳወቂያ ጊዜ ጀምሮ ፍትሃዊ የግብር አሰባበሰብ ስርዓትን ለመዘርጋት፣ ሌብነትና ብልሹ አሰራሮች ለመከላከልና ቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥ በመስጠት ከግብር ከፋዮች የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የተለዩ አዳዲስ አሰራሮችን ወደ ተግባር ለማሸጋገር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልፀዋል፡፡

በቢሮው የችግሮችን ምንጭ በጥናት በመለየት ለመፍታት 24 አዳዲስ አሰራሮች ወደ ተግባር ለማሸጋገር እየሰራ ነው ያሉት ኃላፊው ከኦዲት ውሳኔዎች ጋር በተያያዘ የግልፀኝነት መጓደል የሚስተዋልባቸውን፣ ለሌብነትና ብልሹ አሰራር በር የሚከፍቱ የህግና የአሰራር ክፍተቶች ለማረም የሚያስችሉ አሰራሮች ይተገበራሉ ብለዋል፡፡

በቢሮው የተጀመረው የደረሰኝ ቁጥጥር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለፅ በንግዱ ማህበሰረብ ከደረሰኝ ውጭ በተገዙ ምርቶች በሚመለከት የሚነሱ ጥያቄዎችን በቢሮው ምላሽ መስጠቱንም  አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ ደረሰኝ ሊቀርብባቸው አዳጋች በሆኑ ጉዳዮች ወጪ አያያዝ በተመለከተም በአሰራር ለመመለስ ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡

አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማልማትና ወደ ተግባር በማሸጋገርም የንግዱ ማህበሰረብ ከባለሙያዎች ስነ ምግባር፣ ከሌብነትና ብልሹ አሰራር ፣ ከፍትሃዊ የግብር አሰባሰብ ስርዓት አኳያ ለሚነሱ ቅሬታዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ቢሮው ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘም ለግብር ከፋዮች ምቹ የስራ አካባቢ ለማዘጋጀትና ግብር ከፋዮች ወደ ተቋሙ ሲመጡ በአግባቡ ሊስተናገዱ የሚችሉበት የስራ አካባቢ ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡

የአዲስ ቻምበር   ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ዘሃራ መሐመድ በበኩላቸው ቢሮው የንግዱ ማህበሰረብ ቅሬታዎችን በአሰራር፣ በአደረጃጀትና በቴክኖሎጂ ለመፍታት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት አመስግነው  አሁንም የንግዱ ህብረተሰብ ችግሮችን በመለየት መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የቢሮው አመራር ለዓመታት በንግዱ ማህበሰረብ ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎች  ደረጃ በደረጃ እየተፈቱ እንዲመጡ በማድረግ ረገድ በኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ተናግረው ግብር ከፋዩ አሁንም በሀላፊነት እንዲወጣ ከአዲስ ቻምበር ጋር ተባብሮ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ከንግዱ ማህበረሰብ የሚነሱ ጥያቄዎችን በጥሩ መንፈስና በመተማመን በየደረጃው ያሉ አመራሮች ቢሯቸውን ከፍተው ቅሬታቸውን እንዲቀበሉም ጭምር ፕሬዚዳንቷ አሳስበዋል ።

በዕለቱ የተሳተፉ የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት አመራሮች በበኩላቸው ቢሮው የንግዱ ማህበረሰብ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች በጋራ ውይይት ለመፍታት እየሄደበት ያለው አቅጣጫ  ተስፋ የሚጭር ነው ሲሉ ገልጸውታል::

በዕለቱም ከንግዱ ማህበረሰብ ለተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች የቢሮው ከፍተኛ አመራሮች ምላሽና ማብራሪያም ሰጥተዋል፡፡

wpChatIcon
wpChatIcon