አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2014 የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ለሃገሪቱ የንግድ ስርዓት ማደግና መሳለጥ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት/ አዲስ ቼምበር/ የ75ኛ ዓመት ክብረ በዓሉን በስካይ ላይት ሆቴል እያካሄደ ነው፡፡
በ1939 ዓ.ም የተመሰረተዉ አዲስ ቻምበር ባለፉት 75 ዓመታት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ማከናዉን የገለጹት የምክር ቤቱ ጸኃፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም ምክር ቤቱ ለንግዱ ማህበረሰብ እዉነተኛ ድምጽ መሆኑን በተግባር አረጋግጧል ነዉ ያሉት:: ምክር ቤቱ በተጽእኖዎች ሳይበገር ዘመን ተሸጋሪ ተቋም መሆኑን አሳይቷል ብለዋል ዋና ጸኃፊዉ፡፡
የንድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ በበኩላቸዉ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት 75ተኛ አመት ምስረታዉን ሲያከብር ለመጪው ዘመን የሰነቀውን ተስፋ የሚያመላክትበትና የንግዱ ማህበረሰብ እንደራሴነት ቃልኪዳኑን የሚያድስበት እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
የሃገሪቱን የንግድ የኢንቨስትመንት የኢኮኖሚ ሁኔታዎች እየተከታተሉ የፖሊሲና ሌሎች ምክረሃሳቦችን ለመንግስ በማቅረብ ቻምበር ሃላፊነቱን በተግባር እየገለጸ መምታቱም በመድረኩ ተወስቷል፡፡ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሃሰን መሃመድ እንዳሉትም አዲስ ቻምበር ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ በሀገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ሚና ያለዉን የንግድ ማህበረሰብ በመወከል ጥቅሞቹና መብቶቹ እንዲከበሩ ያላሰለሰ ጥረት አድርጓል ብለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ለሃገሪቱ የንግድ ስርዓት ማደግና መሳለጥ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታዉ የገለጹት፡፡ የአዲስ ቻምበርን የ75 ዓመት ጉዞ የሚያሳይ የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽንም ተከፍቷል፡፡