የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትን ( አዲስ ቻምበር) በተለያዩ ጊዜያት ያገለገሉ የቀድሞ የቦርድ ፕረዚደንቶች በምክር ቤቱ በመገኘት ከወቅቱ የምክር ቤቱ ፕረዚደንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድ ጋር ሰፋ ያለ ምክክርና የልምድ ልውውጥ አካሂደዋል፡፡
በዚህ የትውውቅና የልምድ ልውውጥ መድረክ ላይ የተገኙት የቀድሞ የቦርድ ፕረዚደንቶች አቶ እየሱስ ወርቅ ዛፉ እና አቶ ክቡር ገና ናቸው፡፡
በውይይታቸው ወቅት ወ/ሮ ዘሀራ እንደገለጹት እንደ አቶ ክቡር ገና እና አቶ እየሱስ ወርቅ ዛፉ የመሳሰሉ የቦርድ አመራሮች የምክር ቤቱ ባለውለታዎች እንደሆኑ በመግለጽ በንግድ ምክር ቤቱ ውስጥ ለነበራቸው ቆይታና አስተዋጾ በምክር ቤታቸውና በንግዱ ማህበረሰብ ስም ከፍተኛ ምስጋናን አቅርበዋል፡፡
ንግድ ምክር ቤቱ ዘመናትን እየተሻገረ ዛሬ ላይ እንዲደርስ የትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ ማለፉን ያነሱት ወ/ሮ ዘሀራ የቀድሞ የቦርድ አመራሮች የነበራቸውን ልምድና እውቀት አሁን ላለው የቦርድ አመራር እንዲያካፍሉና ከምክር ቤቱ ጎን በመቆም ከዚህ በኋላ ጠንካራ ተቋም እንዲፈጠር ፕረዚደንቷ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ምክር ቤቱ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ተግዳሮች ሲያጋጥሙት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ክቡር ገና አሁንም ቢሆን ወቅቱን ከግምት ውስጥ ያስገባ ተቋምን እንዲሁም አገልግሎትን እውን ማድረግ እንደሚገባ በተለይም በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋምን መመስረት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ የምክር ቤቱ አመራሮችና የቦርድ አባላት ስኬታማ ለመሆን ከሰራተኞች ጋር ተቀራርቦ መስራት፤ የንግዱን ማህበረሰብ ችግሮች ለመፍታት ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግና ከዚህ ጎን ለጎን ችግሮችን መለየት ፤ ለመፍትሄዎች ቅድሚያ እየሰጡ መስራት እንዲሁም የውስጥና የውጭ ችግሮችን ለይቶ ስልታዊ በሆነ መልኩ ለመፍታት ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ የጠቆሙ ሲሆን በዚህ ጥረት ውስጥ ከምክር ቤቱ ጎን እንደሚቆሙ አስታውቀዋል፡፡
እንደ ቻምበር የመሳሰሉ ተቋማት በግሉ ዘርፍና በመንግስት መካከል አገናኝ ድልድይ እንዲሁም የልማት አጋር እንደመሆናቸው መጠን ንግድ ምክር ቤቱን በቅንነት እና በታማኝነት እንዳገለገሉ የተናገሩት አቶ እየሱስ ወርቅ ዛፉ ምክር ቤቱ ዘላቂ እንዲሆን ህጎችንና ደንቦችን አክብሮ መስራት እንደሚያስፈልግ፤ ተጽእኖ ፈጣሪ ነጋዴዎች ምክር ቤቱን እንዲቀላቀሉ በማድረግ፤ የንግዱን ህብረተሰብ መብትና ጥቅም ሊያስጠብቁ የሚችሉ ህጎችና ደንቦች እንዲወጡ በማድረግ ምክር ቤቱ ሚናውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
በቀጣይም ጠንካራና ተጽእኖ ፈጣሪ ምክር ቤት በሚፈጠርበት አግባብ ላይ ከምክር ቤቱ ጎን እንደሚቆሙ ተናግረዋል፡፡
