በ1939ዓም በቻርተር የተቋቋመው የአዲስ አበባ ንግድ ም/ቤት ዛሬ ላይ የ75 አመት አንጋፋ ተቋም ሆኗል፡፡ ታዲያ ምክር ቤቱ በስኬትና በውጣ ውረድ የታጀበው የ75 አመታት የምስረታ በአሉ ለተለያዩ አጋር አካላት፣ የቻምበር ፕሬዚዳንቶች፣ም/ፕሬዚዳንቶች፣ የቦርድ አባላት እና ሰራተኞች እውቅና በመስጠት ተጠናቀቀ፡፡ ሰኔ 23 ፣2014 በስካይ ላይት ሆቴል በተካሄደው የማጠቃለያ ስነስርአት ከምስረታው አንስቶ የንግድ ምክር ቤቱ በየዘመናቱ ካጋጠመው ፈተናዎችና መሰናክሎች አልፎ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦችና ባለድርሻ አካላት የዋንጫ፣የሜዳልያና ሰርቲፊኬት እውቅና ተሰጥቷል፡፡ ይህ የ75ኛ አመት የምሥረታ በዓሉ ባማረና በደመቀ ሥነስርዓት እንዲከበር በአብይ ኮሚቴ አና ሌሎች 16 ንዑሳን ኮሚቴዎች ተቋቁመው ልዩ ልዩ ተግባራትን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የም/ቤቱን ወጥ ታሪክ የሚያወሳ አዲስ መጽሐፍ ማዘጋጀት ሲሆን መጽሐፉ በገለልተኛ እና ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች የተጻፈ ሲሆን ንግድ ም/ቤቱ በእነዚህ ረጅም አመታት ውስጥ በትውልድ የቅብብሎሽ ሰንሰለት ላይ ያለፈባቸውን መልካም እና ፈታኝ ሁኔታዎችን የሚዘክርና ፣የወደፊቱን የጉዞ አቅጣጫ የሚጠቁም ሰነድ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
ሌላውና አበይት ስራ በ1993 ዓም የተዘጋጀው እና ዘወትር የአዲስ ቻምበር የሬድዮ ፕሮግራም መክፈቻ ሆኖ ሲያገለግል የቆየው እና በሕዝብ ጆሮ የተለመደው ‘ ራዕያችን’ የተሰኘው ዝማሬ መሠረቱን ሳይለቅ በተሻለ የድምጽ ጥራት እና ባማረ ሙዚቃዊ ቅንብር እንደገና ዘምኖ፣ተሻሽሎና ተዘጋጅቶ እንዲወጣ ተደርጓል ተብሏል፡፡
በተለያዩ የመንግስት ስርአቶች ውስጥ የንግዱ ህብረተሰብ እና ምክር ቤቱ ያሳለፏቸውን ውጣ ውረዶች፣ እድሎቹና ተስፋዎቹን የሚያሳይ ‘የነጋዴው ዋርካ’ በሚል ዶክመንታሪ ፊልም በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተዘጋጅቶ ለተመልካች በቅቷል፡፡
በአሉ በተለያዩ የንግድና ኢንቨስትመንት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ታላላቅ የፖሊሲ ፓናሎችና ሲምፖዚየሞች የተካሄዱበትም ነበር፡፡ በስካይ ላይት ሆቴልና በሂልተን ሆቴል ለ3 ቀናት ከተካሄዱት ፓናሎቹና ሲምፖዚየሞቹ መካከል በኢትየጵያ የግሉ ዘርፍ ልማትና ከባቢ የፖሊሲ ሁኔታዎች፣ ህገወጥ ንግድና የተወዳዳሪነት ፈተናዎች፣ የህጎችና ደንቦች አወጣጥ በግሉ ዘርፍ ልማት ፣ በሴቶች የሚመራ የቢዝነስ አመራር፣ የሶሻል ኢንተርፕራይዝ እድሎችና ፈተናዎች እንዲሁም ዛሬ የተካሄደው የንግድ ማህበራትና ተቋማት በኢትየጰያ ኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸው ሚና የመሳሰሉት ርእሶች ይገኙበታል፡፡ በእነዚህንም ፓናሎች ታዋቂ ምሁራን፣የፖሊሲ አውጪዎች እና የግሉ ዘርፍ ተዋንያን ሀሳባቸውን አቅርበዋል፡፡
በአጠቃላይ ይህ ክብረ በአል ምክር ቤቱ በመጪው ዘመን የሰነቀውን ተስፋ የሚያመላክትበትና የንግዱ ማህበረሰብ እንደራሴነቱን ከወትሮው በተለየ ሁኔታ የሚያሳይበት እና ካልኪዳኑን የሚያድስበት መሆኑን ንግድ ምክር ቤቱ ገልጿል፡፡ በተለይ በአሉ እንዲህ በሰመረ ሁኔታ እንዲከበር አስተዋጽኦ ላበረከቱ አጋር ተቋማት ልባዊ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡