የአዲስ ቻምበር የቦርድ አባላት፣ ማኔጅመንት እና ሠራተኞች የመቄዶንያ የአረጋውያን እና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከልን ጎበኙ

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት(የአዲስ ቻምበር) የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት እና የጽ/ቤቱ ማኔጅመንት እና ሠራተኞች  የመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከልን ጎበኙ፡፡

በጉብኝቱ ወቅት ለአረጋውያኑ እና የአዕምር ህሙማኑ የሚሰጣቸውን የሕክምና፤የምግብና የንጽሕና አገልግሎት የቻምበሩ መሪዎች እና ሠራተኞች ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡

በ2004 ዓ፡ም የተመሠረተው የመቄዶንያ መርጃ ማዕከል ምንም ደጋፊ እና ጠዋሪ የሌላቸውን እንዲሁም  የሰው ድጋፍ የሚሹ አረጋውያን ከወደቁበት በማንሳት በማዕከሉ እዲያገግሙ የመጠለያ፤ የምግብ፤የሕክምና እና የሥነ ልቦና ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

የአዲስ ቻምበር ፕሬዝደንት ወ/ሮ ዘሐራ መሀመድ ማዕከሉ የሚያከናውነው ሰብዓዊ እና የበጎ አድራጎት ጥረቶች የንግዱን ሕብረተሰብ በማስተባበር የተቻለውን ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡

የንግዱ ሕብረተሰብ እንደማንኛውም የሕብረተሰብ ክፍል በተለያዩ ወቅቶች ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ አደጋዎች በወገኖቻችን ላይ ሲከሰቱ የንግዱ ሕብረተሰብ  በገንዘብ እና በቁሳቁስ ወዘተ ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ ቆይቷል ብለዋል፡፡

የመቄዶንያ አረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢንያም በለጠ በበኩላቸው የአዲስ ቻምበር ፕሬዝደንት ወ/ሮ ዘሐራ ለማዕከሉ በርካታ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸው በቀጣይ የንግዱን ሕብረተሰብ ማዕከሉ በሚያደርጋቸው የገቢ ማሰባሰቢያ ሁነቶች ላይ በስፋት  እንዲሳተፍ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

ማዕከሉ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ የሚያነሳቸው እና የሚረዳቸው ተረጂዎች ራሳቸውን መርዳት የማይችሉበት ደረጃ የደረሱ ተረጂዎች በመሆናቸው በተለይ በቀን 3 ጊዜ የሚቀየሩት  አዋቂዎች ዳይፐር፤የሳሙናና የሴቶች የንጽሕና መጠበቂያ ግብዓቶች  እጥረት እያጋጠመው መሆኑን  አቶ ቢንያም አስታውሰው ዛሬ ላይ  በማዕከሉ የሚረዱ ከ8000 በላይ ለሚሆኑ ወገኖች ለምግብ ብቻ በቀን እስከ 2.5 ሚሊየን ብር ወጪ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በየጊዜው ከሚጨምረው የተረጂዎች ቁጥር አንጻር የንግዱ ሕብረተሰብ የበኩሉን አስተዋጽኦ አንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአዲስ ቻምበር ዋና ጸሐፊ ዶ/ር መሠረት ሞላ በበኩላቸው የንግድ ም/ቤቱ  ሠራተኞች አረጋውያንን በመመገብ፤በመንከባከብ ለማዕከሉ የስትራተጂ ዕቅዶችን በመቅረጽ፤በሥልጠና እና  ሌሎች የቴክኒክ ድጋፎችን ለማድረግ ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡

መቄዶንያ የአረጋውያንና አዕምሮ መርጃ ማዕከል ከ8 ሺህ 500 በላይ ተረጂዎችን በተለያዩ 45 የክልል ቅርንጫፍ ማዕከላት ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን በበጎ አድራጊዎች ከሚያገኘው ልገሣ በስተቀር ምንም ዓይነት የገቢ ምንጭ አንደሌለው ተነግሯል፡፡

wpChatIcon
wpChatIcon