ሉናር ኢንተርናሽናል ኮሌጅ የንግድ ባህል ስነምግባር ላይ ያተኮረ የመጀመሪያውን አመታዊ የጥናት አውደርእይ በዛሬው እለት አካሒዷል፡፡
በስድስት በተመረጡ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የተሰሩ ጥናቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ጥናቶቹ በአርብቶ አደር አካባቢዎች በሚሰጥ የኢንሹራንስ እና ባንክ አገልግሎት ፤ የተማሪዎች በቢዝነስ ዘርፍ የመግባት ፍላጎትና ውጤታማነት እንዲሁም የተቋማት ብድርን በአግባቡ የማግኘት ሁኔታዎች ላይ ያተኮሩ እና ሌሎች ጉዳዮችንም ያካተቱ ናቸው፡፡
የሉናር ኢንተርናሽናል ኮሌጅ ፕሬዝደንት ዶ/ር ታሪኩ አቶምሳ እንደገለጹት የንግድ ባህላችን በስነምግባር የታነጸ እንዲሆን በየፈርጁ ችግሮችን ለይቶ በጥናት የተደገፈ መፍትሔ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ እድገት ከሚለካባቸው መስፈርቶች አንዱ ኢኮኖሚ መሆኑን ያነሱት ዶ/ር ታሪኩ ለዚህ የሚረዳ በቂ የተማረ የሰው ሀይል ለዘመናዊ ቢዝነስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በዚህ ረገድ በዘርፉ የሰለጠኑ ከየትምህርት ተቋማቱ ተመርቀው ገበያውን ለመቀላቀል የተዘጋጁ ተማሪዎች ላይ መስራት አስፈላጊ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ከውይይቱ የሚሰበሰቡትን ግብረመልሶች በአንድ ሰነድ በማደራጀት የአዲስ አበባ ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤትን ጨምሮ ለሚመለከታቸው አካላት እንደሚቀርብ ጠቁመዋል፡፡
በውይይቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የአዲስ አበባ ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ዋና ጸሀፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በበኩላቸው በውይይቱ ላይ የቀረቡ ጥናቶች ምክረ ሀሳቦችን እና ከተወያዮች የተነሱ ሀሳቦችን ም/ቤቱ ተቀብሎ እንደሚሰራባቸው አረጋግጠዋል፡፡