አዲስ ቻምበር የአባላት ቀንን አስመልክቶ የምስጋና እና የእውቅና መርሃግብር አካሄደ

80 አመት ያስቆጠረው የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አባላቶቹን አመስግኗል፡፡

በዝግጅቱ የምክር ቤቱ የቦርድ አባላት እና ማኔጅመንት፡የመንግስት ባለድርሻዎች እንዲሁም አባላት እና አጋር ተቋማት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

በአባልነት እና በአጋርነት አብረውት ሲሰሩ የቆዩ ተቋማትም ከንግድ ምክር ቤቱ ጋር በነበራቸው የስራ ግንኙነቶችን አስመልክቶ ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡

በአጋርነት ረዘም ላለግዜ ከንግድ ምክር ቤቱ ጋር አብረው መስራታቸውን ያነሱት የሳይፕ( CIPE) የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር አቶ ሃይለ መለኮት አስፋው አዲስ ቻምበር በአባልነት ላይ ከተመሰረቱ ተቋማት እና አብረዋቸው ሊሰሩ ከሚችሉት ውስጥ በተለያየ አቅጣጫ አቅም ያለው እና መስፈርቶችን የሚያሟላ መሆኑን እንዲሁም ከቻምበር ጋር በአጋርነት በመስራት በተለይ በመንግስት እና የግሉን ዘርፍ ለማቀራረብ በተደረገው ጥረት በተገኙ ውጤቶች ደስተኛ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የአፍሪኮም ቴክኖሎጂ መስራች የሆኑት አቶ ባህሩ ዘይኑ በበኩላቸው ከቻምበር ጋር የነበራቸው የስራ ግንኙነትን አስመልክቶ በሰጡት ምስክርነት በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ ከመሆናቸው አንጻር ምክር ቤቱ ለአባላቱ ሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ዲጂታል በማድረግ እረገድ የመሳተፍ እድል እንደነበራቸው እና ንግድ ምክር ቤቱ በሚያቋቁማቸው ኮሚቴዎች በተለያዩ ሃላፊነቶች መሳተፋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የኤስ ኤ ኬ የስልጠናና የማማከር አገልግሎት ስራ አስኪያጅ ዶ/ር አደራ አብደላም በበኩላቸው የምክር ቤቱ አባል ከመሆን እና ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች ተጠቃሚ ከመሆን ባሻገር በጋራ በርካታ ስራዎችን ከቻምበር ጋር መስራታቸውን አንስተዋል፡፡

የምክርቤቱ የአባላት ልማት እና ድጋፍ መምሪያ በየአመቱ አባላቱን የሚያመሰግንበት መርሃ ግብር እንደሚያዘጋጅ የሚታወቅ ሲሆን የዘንድሮም በርካታ አባላት በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

የተለያዩ አባላትና አጋር አካላት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ከአዲስ ቻምበር ምክትል ፕሬዚዳንት ኢንጂነር አበበ ጉርሜሣ እጅ የእውቅና ሰርቲፊኬት ተበርክቶላቸዋል ።

የአዲስ ቻምበር የአባላት እና የአጋር አካላት የምስጋና ቀን በፓናል ውይይት የታጀበ ሲሆን የንግድ ምክር ቤቶች ሚና በኢኮኖሚ ውስጥ በሚል ርእስ የተለያዩ ባለሙያዎች እና የመንግስት ሐላፊዎች የመነሻ ፅሁፍ አቅርበዋል ።

ከ100 በላይ ተሳታፊዎች በመድረኩ ላይ የታደሙ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል ።