የጋራ ስምምነቱ የንግዱን ማህበረሰብ፣ አዲስ ቻምበርን፣ ህብረተሰቡን እና ስራ ፈጣሪዎችን በላቀ ሁኔታ እንዲጠቅም ተደርጎ የሚተገበር ነው።
ለንግዱ ማህበረሰብ የተሻለ እና ምቹ የንግድ ከባቢ ሁኔታ እንዲፈጠርና የስራ ፈጠራ ስነምህዳርን ለማሻሻል የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከ 3 ባለድርሻ ተቋማት ጋር የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል ፡፡
የኢትዮጵያ የኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢኒስቲትዩት ፣ የአዲስ አበባ ንግድ ስራዎች ድርጅት እና አዋሽ ባንክ ናቸው የመግባቢያ ሠነድ የተፈራረሙት ።
በአዲስ ቻምበር በኩል የጋራ መግባቢያ ስምምነቱን የተፈራረሙት የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ዘሃራ መሃመድ ናቸው።
የጋራ መግባቢያው ለመካከለኛ እና አነስተኛ የንግድ ተቋማት ስለሚኖር የገንዘብ አቅርቦት ፣ በስራ እድል ፈጠራና ክህሎት ፤ በምርት ስርጭት ላይ የግሉ ዘር ፍ ስለሚኖረው አስተዋጽኦ ፣እድልና የዋጋ ማረጋጋት ሚናን ለማከናወን የሚያስችሉ መሆናቸው ተጠቁሟል ።
ምክር ቤቱ ከተቋማቱ ጋር በገባው ስምምነት መሰረትም ስራዎቹን በጽ/ቤቱ በኩል ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተጠቅሷል፡፡
በኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩቱ በኩል ዋና ስራ አስፈጻሚው ዶ/ር ሐሠን ሁሴን፤ በአዲስ አበባ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን በኩል ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ መስፍን አሰፋ እንዲሁም በአዋሽ ባንክ ደግሞ አቶ መልካሙ ታደሰ ተፈራርመዋል ።
አዲስ ቻምበር ከአለም አቀፉ የግል ኢንተርፕራይዝ ማእከል ጋር በመተባበር በገንዘብና በመስሪያ ቦታ(በመሬት) አቅራቦት ለግሉ ዘርፍ ልማት በሚል ታላቅ የመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ በካፒታል ሆቴል ተካሂዷል።
በምክክር መድረኩ ላይ ጥናታዊ ፅሁፎችን እና ምላሾች ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከብሄራዊ ባንክ ፣ከአዲስ አበባ ኢንዱስትሪ ቢሮ፣ ከግሉ ዘርፍና ከምሁራን የተውጣጡ ሀላፊዎች እና ከፍተኛ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል ።
በመድረኩ ላይ ከ150 በላይ የሚመለከታቸው የመንግሥት ሐላፊዎች ፣ የግሉ ዘርፍ ተወካዮች ፣ የልማት አጋሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል ።
