አዲስ ቻምበር እና የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ አብረው መስራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መከሩ ፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ እያደረገ ባለው የሪፎርም ስራዎች ንግድ ቢሮው ትብብር እንደሚያደርግ የቢሮው ሀላፊ ክብርት ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ ገልፀዋል፡፡
(መስከረም 23፤2017 ፤ አዲስ ቻምበር) በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት/ አዲስ ቻምበር/ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የተመራ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ቡድን ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ሃላፊ ከክብርት ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅና ከሌሎች የቢሮው አመራሮች ጋር በጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ውይይት አካሂደዋል፤፤
አዲስ ቻምበር የግሉን ዘርፍ በማጠናከር ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን በመስጠትና በመንግስትና በንግዱ ሕብረተሰብ መካከል እንደ አገናኝ ድልድይ በመሆን የሚሰራውን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል የንግድ ቢሮው ሀላፊ ክብርት ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ አሳስበዋል ፡፡
ቢሮው ከንግድ ምክር ቤቱ ጋር አብሮ ሊሰራባቸው በሚችልባቸው ንግድ ነክና በሌሎች ስትራቴጂክ ጉዳዮች ዙሪያ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል ፡፡
ስምምነቱን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሃቢባ ሲራጅ እና የአዲስ ቻምበር ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሽንቁጤ ፈርመዋል ፡፡
የአዲስ ቻምበር ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሽንቁጤ እንደተናገሩት ንግድ ምክር ቤቱ በአዋጅ የተቋቋመ እና ነጋዴውን ከመንግስት ጋር እንደ አገናኝ ድልድይ ሆኖ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማቀላጠፍ ከንግድ ቢሮው ጋር በይበልጥ ተቀራርቦ መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል ፡፡
እንደ ወ/ሮ መሰንበት ገለፃ ንግድ ምክር ቤቱ ከንግድ ቢሮው ጋር ጠንካራ ግንኙነትን በማሻሻል፤የግልና የመንግስት የምክክር መድረክ በመፍጠር በከተማዋ ዘመናዊ የንግድ አሰራርን ለማሰፈን መስራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል ፡፡
የንግድ ምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ፋሲካው ሲሳይ በበኩላቸው ንግድ ምክር ቤቱ በሪፎርም ስራ ላይ መሆኑን ጠቁመው ንግድ ምክር ቤቱ የተቋቋመለትን ዋነኛ የንግድና ኢንቨስትመንት ማስተዋወቅ ስራና አላማን አጠናክሮ ለማስቀጠልና ለንግዱ ህብረተሰብ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችል ቁመና እንዲኖረው ተደርጎ እንዲዋቀር የሚያስችል አሰራር እየተዘረጋ መሆኑን ለቢሮው አመራሮች አብራርተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሃቢባ ሲራጅ በበኩላቸው ያለ ግሉ ዘርፍ ተሳትፎና ንግድ ምክር ቤቱ እገዛ መንግስት ብቻውን ውጤታማ ሊሆን እንደማይቻል ጠቅሰዋል፡፡
በመሆኑም የከተማዋን የንግድ ህብረተሰብ የሚመጥን ንግድ ምክር ቤት ለማድረግ በሚደረገው ርብርብ መንግስት በተለይም ንግድ ቢሮው የቅርብ እገዛ እንደሚያደር ተናግረዋል፡፡
በከተማዋ ከ400ሺህ በላይ የሚሆኑ ነጋዴዎች ንግድ ፍቃድ አውጥተው እየተንቀሳቀሱ መሆንኑን ጠቁመው ንግድ ምክር ቤቱ አባላቱን አሁን ካለበት17 ሺ በላይ ማሳደግ እና አገልግሎት መስጠት መቻል አለበት ብለዋል፡፡
ንግድ ምክር ቤቱ የአባላቱን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያደርገውን ስራ ንግድ ቢሮው እንደሚደግፍ ገልፀው ከተማዋ ይበልጥ ልታድግና ልትለማ የምትችለው ጠንካራ የንግድ ማህበረሰብ ሲፈጠር መሆኑን አፅዕንዖት ሰጥተው ተናግረዋል ፡፡
ለዚህም የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ከንግድ ምክር ቤቱ ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡
wpChatIcon
wpChatIcon