(አዲስ ቻምበር ሰኔ 11 ቀን 2018 አ.ም ) የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት (አዲስ ቻምበር) ከቦሌ፣ ከየካ እና ከለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞች ለተውጣጡ አነስተኛና መካከለኛ ነጋዴዎች እንዲሁም ለምክር ቤቱ የክፍለ ከተማ ተወካዮች በንግድ አመራርና ስነ-ምግባር ዙሪያ ያተኮረ ስልጠና ሰጠ።
በስልጠናው መርሃ ግብር ላይ የንግድ ምክር ቤቱ ዋና ጸኃፊ አቶ ዘካርያስ አሰፋ፣ እና ሌሎች የምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
የስልጠናውን መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የምክር ቤቱ ዋና ጸኃፊ አቶ ዘካርያስ አሰፋ፣ ንግድ ምክር ቤቱ የንግድ ዘርፉ በእውቀት እንዲመራና በየወቅቱ የሚወጡ አለም አቀፋዊ ለውጦችን ከግምት ያስገባ እንዲሆን የተለያዩ የስልጠና መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
አክለውም ይሄኛውን ስልጠና ልዩ የሚያደርገው ምክር ቤቱ በክፍለ ከተማና በወረዳ ደረጃ የሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ የንግድ አንቀሳቃሾችን ብቃት ለመገንባት አስቀድሞ ዳሰሳዎችን በማካሄድ ስልጠናው መሰጠቱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ስልጠናውም ቀጣይነት ያለው መሆኑን እና መርሃ ግብሮቹ በንግድ አመራርና በስራ ፈጠራ ላይ ትኩረት ማድረጋቸው ከንግድ ጋር የተያያዙ ግንዛቤዎችን ለማስጨበጥ ያለሙ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የምክር ቤቱ ምክትል ዋና ጸኃፊ አቶ ካሳሁን ማሞ በበኩላቸው፣ ንግድ ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም ከነበሩት አባላቱ በተጨማሪ የአባላት ቁጥሩን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ምክር ቤቱ በርካታ የከተማዋን ነጋዴዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚና ተደራሽ ለማድረግ እያደረገ የሚገኘውን የተጠናከረ ስራ እና እየተጓዘበት ያለውን ርቀት ለስልጠናው ተሳታፊዎች በስፋት አስረድተዋል።
ስልጠናውን የሰጡት የስልጠና ባለሞያው አቶ ሃብታሙ ፋንቱ በበኩላቸው፣ በንግድ አመራር ላይ መሰረታዊ እውቀትና ክህሎት መኖር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል። ይህንን እውቀት ለማሟላትም መሰል ስልጠናዎች ቁልፍ ሚና እንደሚጫወቱ የጠቆሙ ሲሆን፣ የንግድ አመራር ክህሎት ለአንድ ንግድ ቀጣይነትና ስኬት መሰረት መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህ የስልጠና መርኀ ግብር ላይ የማጠቃለያ መልእክታቸውን ያስተላለፉት የምክር ቤቱ ምክትል ዋና ጸሀፊ አቶ ጀማል ሰኢድ መሰል ስልጠናዎች በቀጣይ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉና በተለይም ፍላጎትን መሰረት ያደረጉ የስልጠና አይነቶች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አክለው አብራርተዋል፡፡
አዲስ ቻምበር የግሉ ዘርፍ አገልጋይ
