አዲስ ቻምበር ለቀድሞ የዳይሬክተሮች የቦርድ አባላቱ የምስጋና መርሀግብር በማዘጋጀት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናውን አቀረበ፡፡

‘አዲስ ቻምበር ባሳለፋቸው በርካታ አመታት ም/ቤቱን ከምንም አንስተው ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ያደረሱ ትጉኅ የቀድሞ አመራሮቹን እያመሠገነ እና በታራክ ማኅደሩ እያሰፈረ ይቀጥላል’ ፤ ወ/ሮ ዘሐራ መሐመድ የአዲስ ቻምበር ፕሬዚዳንት

የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት/አዲስ ቻምበር/ የግሉን ዘርፍ በማጠናከር በሀገሪቱ ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ የበኩሉን ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ በተለያዩ እድሎችና ተግዳሮቶች ውስጥም ሆኖ እያስመዘገበ ላለው ተቋማዊ ጥንካሬ እና አሁን ለደረሰበት ደረጃ ለቀድሞዎቹ የቦርድ አባላት አሰተዋጽኦ ምስጋናውን አቅርቧል ፡፡

በኢንተርላግዠሪ ሆቴል በተካሄደው የምስጋና መርሀግብር ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የወቅቱ የአዲስ ቻምበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድ እንደተናገሩት የመላውን የንግዱን ማህበረሰብ በተለይም የአባሎቻችንን ፍላጎት ለማርካት ደከመኝ፣ሰለቸኝ ሳይሉ በጽናት በማገልገል ላሳዩትት ቁርጠኝነት ለቀድሞዎቹ አመራሮች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡ ፤

ፕሬዚዳንቷ አክለውም የቀድሞዎቹ አመራሮች ‘ያለፋችዃቸው የአመራር አመታት በየኔነትና በባለቤትነት ስሜት የሰራችዃቸው ስራዎች የየራሳቸው ምእራፎችና አነሰም በዛም የራሳቸው ታሪክ እንዲኖራቸው ሆኗል’ ብለዋል፡፡

በዚህ አጋጣሚ አዲስ ቻምበር ባሳለፋቸው ስምንት አስርት አመታትም ም/ቤቱን ከምንም አንስተው ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ያደረሳችሁ  ትጉኅ አባላቶቹ በታራክ ማኅደሩ አስፍሮ እያተካካ ይቀጥላል ብለዋል።

ወ/ሮ ዘሀራ በስተመጨረሻም ለቀድሞ አመራሮቹ ባስተላለፉት መልእክት ‘በአባልነታችሁ እና ከአመራር ተሞክሯችሁ ለምክር ቤቱ ያላችሁን ድጋፍ እንድታጠናክሩና የበኩላችሁን አስተዋጽኦ በማበርከት አሻራችሁን እንድታኖሩ አሁንም በምክር ቤቱ ስም ጥሪ ሳቀርብላችሁ በታላቅ ደስታ ነው’ ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል ፡፡

የቀድሞው የአዲስ ቻምበር ሁሉም የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት እንደተናገሩት ምክር ቤቱ በሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች እና ተጽእኖዎች ሳይሸነፍ ልምድና ተሞክሮውን እየቀመረ ተግዳሮቶቹን የመቋቋም አቅሙን  እያዳበረ በቀጣይም አገልግሎቱን እና ተደራሽነቱን ለማስፋትት ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ አሁንም ከምክር ቤቱ ጋር በጋራ እንሰራለን ብለዋል፡ ፡

የቀድሞ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት በአመራር ዘመናቸው ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የምስጋና የምስክር ወረቀትና ሌሎች ማስታወሻዎችን ከወቅቱ የአዲስ ቻምበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድና ከተ/ዋና ፀሀፊ ከአቶ ዘካሪያስ አሠፋ እጅ ተበርክቶላቸዋል፡ ፤

በምስጋና መርሀግብሩ ላይ የወቅቱ እና የቀድሞ የአዲስ ቻምበር የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት እንዲሁም የማኔጅመንት አባላት ተገኝተዋል፡ ፡