የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት (አዲስ ቻምበር) የዳይሬክተሮች ቦርድ አመራር አቶ ካሳሁን ማሞን እና አቶ ጀማል ሰይድን ምክትል ዋና ፀሐፊ አድርጎ መሾሙን አስታወቀ።
አዲሶቹ ሀላፊዎች በቅርቡ ዋና ፀሐፊ ሆነው ከተሾሙት አቶ ዘካርያስ አሰፋ ጋር በመሆን የምክር ቤቱን ስልታዊ ግቦች ለማሳካት በቅንጅት የሚሰሩ ይሆናል።
አቶ ካሳሁን ማሞ የንግድ ልማት እና የአድቮኬሲ ዘርፍ ምክትል ዋና ፀሐፊ ሆነው የተሾሙ ሲሆን አቶ ካሳሁን ባለፉት 11 ዓመታት በምክር ቤቱ ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ማለትም የአድቮኬሲ እና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተርና የውጭ ግንኙነትና ሚዲያ ስራ አስኪያጅ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (EBC) አንጋፋ የቢዝነስ እና ኢኮኖሚ ኤዲተር እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ምጣኔ ሐብት መምህር ነበሩ።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በልማት ጥናት (Development Studies) የማስተርስ ዲግሪያቸውን ከ17 አመታት በፊት መያዛቸው ለዘርፉ ትልቅ እሴት እንደሚጨምር ይታመናል።
በተመሳሳይ አቶ ጀማል ሰይድ የአባላት እና ተቋማዊ ልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ፀሐፊ ሆነው ተሹመዋል። አቶ ጀማል በተለያዩ የግል ተቋማት ውስጥ በዋና ስራ አስፈጻሚነት እና በምክትልነት ከፍተኛ የአመራር ልምድ ያላቸው ሲሆን፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም በዲንነት እና በመምህርነት አገልግለዋል።
በትምህርት ዝግጅታቸው በሂሳብ አያያዝ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ፣ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በልማት ጥናት የማስተርስ ዲግሪያቸውን አግኝተው ለዚህ የኃላፊነት ቦታ በቅተዋል።
እ.ኤ.አ በ1939 የተመሰረተው አዲስ ቻምበር በኢትዮጵያና በአፍሪካ አንጋፋ የንግድ ምክር ቤት ሲሆን፣ የዓለም የንግድ ምክር ቤቶች ፌዴሬሽን አባልም ነው።
