በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ የንግድ ምክር ቤቶች ታሪክ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፈው አዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት/ አዲስ ቼምበር/ የ75ኛ ዓመት ክብረ በዓል መክፈቻውን የፊታችን ማክሰኞ ከጧቱ 3፡00 ጀምሮ በስካይ ላይት ሆቴል ያካሂዳል፡፡
ንግድ ምክር ቤቱ የተመሰረተበት 75ኛ ዓመት ክብረ በዓል ከሰኔ 21-23 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ በድምቀት የሚከበር ሲሆን በበዐሉ ላይ የምክር ቤቱ አባላት፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ሚኒስትሮች፣ ምሁራን ፣ የልማት አጋሮች፣ ሚዲያዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ከ 400 በላይ እንግዶች ይታደማሉ፡፡
ምክር ቤቱ በስኬትና በውጣ ውረድ የታጀበ የ75 አመታት ታሪካዊ ጉዞውን የሚዘክርበትን፣ የወቅቱን ተጨባጭ ሁኔታውን የሚያሳይበትንና የመጻይ ዘመን ጉዞውን የሚተልምበትን ይህን ታሪካዊ በዓል በተለየና ታሪካዊ በሆነ መልኩ ለማክበር እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ታሪክ የኢትዮጵያ ዘመናዊ የንግድ ታሪክ ነው ብሎ የሚያምነው አዲስ ቼምበር ከምስረታው አንስቶ የግሉ ዘርፍና የንግድ ምክር ቤቱ በየዘመናቱ ካጋጠሟቸው ፈተናዎችና መሰናክሎች አልፈው አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦችና ባለድርሻ አካላት እውቅና ከመስጠት ባለፈ፣ በተለያዩ የንግድና ኢንቨስትመንት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ታላላቅ የፖሊሲ ፓናሎችና ሲምፖዚየሞች፣ የምክር ቤቱን የ75 አመታት ጉዞ የሚያስቃኙ ዘጋቢ ፊልም እና ታሪካዊ መፅሃፍ የሚመረቁበት ሲሆን የፎቶ አውደ ርእይ እና የውይይት መድረኮችንም የሚያጠቃልል ይሆናል፡፡
በስካይ ላይትና ሂልተን ሆቴሎች ለ 3 ቀናት ከሚካሄዱት ፓናሎቹና ሲምፖዚየሞቹ መካከል በኢትየጵያ የግሉ ዘርፍ ልማትና ከባቢ የፖሊሲ ሁኔታዎች፣ ህገወጥ ንግድና የተወዳዳሪነት ፈተናዎች፣ የህጎችና ደንቦች አወጣጥ በግሉ ዘርፍ ልማት ፣ የቢዝነስ መጻኢ እድሎች እንዲሁም የንግድ ማህበራትና ተቋማት በኢትየጰያ ኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸው ሚና የመሳሰሉት ርእሶች ይገኙበታል፡፡
በእነዚህንም ፓናሎች ታዋቂ ምሁራን፣የፖሊሲ አውጪዎች እና የግሉ ዘርፍ ተዋንያን የመነሻ ጽሁፍ ያቀርባሉ፡፡
በክብረ በአሉ መክፈቻ የአዲስ ቻምበርን ታሪክን የሚዘክር መጽሐፍም ታትሞ ለምረቃ እና ለንባብ የሚበቃ ይሆናል፡፡
መጽሐፉ በገለልተኛ እና ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች የተጻፈ ሲሆን ንግድ ም/ቤቱ በእነዚህ ረጅም አመታት ውስጥ በትውልድ የቅብብሎሽ ሰንሰለት ላይ ያለፈባቸውን መልካም እና ፈታኝ ሁኔታዎችን የሚዘክር ሲሆን የወደፊቱን የጉዞ አቅጣጫ የሚጠቁም ጭምር ነው ተብሏል፡፡
የምክር ቤቱን 75 አመታት የሚያስቃኝ የቴቪ ዶክመንታሪ ፊልምም ተዘጋጀ ሲሆን በቀጣዩ ሰኞ ምሽት በፋና ቴቪ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በ1993 ዓም የተዘጋጀው እና ዘወትር የአዲስ ቻምበር የሬድዮ ፕሮግራም መክፈቻ ሆኖ ሲያገለግል የቆየው እና በሕዝብ ጆሮ የተለመደው ‘ ራዕያችን’ የተሰኘው ዝማሬ መሠረቱን ሳይለቅ በተሻለ የድምጽ ጥራት እና ባማረ ሙዚቃዊ ቅንብር እንደገና ተዘጋጅቶና ተሻሽሎ የሚቀርብ ይሆናል፡፡
የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ የሚደገፈው በንግዱ ማኅበረሰብ ንቁ ተሳትፎ፣ በመንግሥት እና በንግዱ ማኅበረሰብ መካከል በሚፈጠር መተማመን ስለመሆኑ የንግድ ምክር ቤቱ በጽኑ አምናለሁ ብሏል፡፡
የእስከ አሁኑን ጨምሮ ምክር ቤቱ በ 75 አመታት እድሜው በንግዱ ህብረተሰብ የተመረጡ 19 ፕሬዚዳንቶች መርተውታል ፡፡
ከነዚህ መካከል አቶ ገብረስላሴ ኦዳ፣ የቀድሞ የንግድ ባንክ ስራ አስኪያጅና የብሄራዊ ባንክ ገዥ የነበሩት ዶክተር ተፈራ ደግፌ፣የማስታወቂያው ባለሙያ አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ፣አቶ ክቡር ገና፣ የህብረት ኢንሹራንስ መስራቹ አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ፣አቶ አያሌው ዘገየ፣ አቶ ኤሊያስ ገነቲና የወቅቱ እና ብቸኛዋ ሴት ፕሬዚዳንት መሰንበት ሸንቁጤ ይገኙበታል።
የአዲስ አበባ ንግድ ም/ቤት በ1939 ዓ.ም በቀዳማዊ አፄ ኀይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት በአዋጅ የተቋቋመ ተቋም ነው።
ጀግኖች አባቶቻችን የፋሺስት ወረራን ቀልብሰው ኢትዮጵያን እንደገና በእግሯ ለማቆም በሚታትሩበት በ1930ዎቹ መጨረሻ ላይ በሀገር ፍቅር ማኅበር ታቅፈው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ነጋዴዎች ለምክር ቤቱ መቋቋም ምክንያቶች ነበሩ፡፡
ዬኔው የአዲስ አበባ ነጋዴዎች፣ ምክር ቤታቸውን ያቋቋሙበት ምክንያትና ዓላማ በንግዱ ማኅበረሰብና በመንግሥት መካከል አገናኝ ድልድይ ሆነው ህጋዊ አግባቦችን ሁሉ በመጠቀም የሀገራችንን የንግድ ሥራን ለማሻሻል የሚበጁ ሀሳቦችን ለማቅረብ እንደነበር ይታወቃል::
የአሁኑ የ 75 አመት የበዓል አከባበር ያለፈው ታሪክ የሚዘከርበት ብቻም ሳይሆን፣ ወቅታዊ ዕድሎችና ፈተናዎች የሚንጸባረቁበት እና በቀጣይም ምክር ቤቱ ዘመኑን የሚመጥኑ አማራጭ የፖሊሲ ምክረ ሀሳቦችን ከአባላቱ ጋር በመሆን ለሚመለከተው በማቅረብና የመፍትሔ አካል በመሆን የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በመቅረፍ ረገድ በቀጣይነት ሊያከናውናቸው ያሰባቸውን ተግባራት የሚያስተዋውቅበት እንደሚሆንም ንግድ ም/ቤቱ አስታውቋል፡፡