የአዲስ ቻምበር 6ኛው የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ “የንግድ ምክርቤቶች እና የዘርፍ ማህበራት ሚና በኢኮኖሚና በአለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ላይ” በሚል ከ100 በላይ የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት በኢንተርላግዠሪ ሆቴል ተካሂዷል ።
አዲስ ቻምበር ከአጋሩ የአለምአቀፉ የግል ኢንተርፕራይዝ ማእከል ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ የአዲስ ቻምበር ከፍተኛ አመራሮች ፣ የመንግሥት ሐላፊዎች፣ የማህበራት አመራሮች ፣ አባል ኩባንያዎች፣ ምሁራንና ባለሙያዎችና አጋር ባለድርሻ አካላት ተገኝተው በርእሰ ጉዳዪ ላይ ሰፊ ምክክር አድርገዋል።
በምክክሩ ላይ እንደተገለፀው የግሉ ዘርፍ ተቋማት ማለትም ንግድ ምክር ቤቶችና የዘርፍ ማህበራት የንግዱንና የአምራቹን ማህበረሰብ በመወከል የሚመሰረቱ ተቋማት ሲሆኑ የህልውናቸው መሰረትም አባላቶቻቸው መሆናቸውን በደምብ መረዳት ያስፈልጋል ተብሏል ፡፡
እነዚህ ተቋማት ግለሰብ ነጋዴን ጨምሮ በልዩ ልዩ የንግድ ስራዎች ላይ የተሰማሩ የንግድ ድርጅቶችን በአባልነት የሚያካትቱ ሲሆኑ ለአባላቶቻቸው የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠትና ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር በቅርበት መወያየት ተቀዳሚው ዓላማቸው ሊሆን እንደሚገባ በምክክሩ ላይ የተገኙት የፅሁፍ አቅራቢዎች አመላክተዋል ፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ የግሉን ዘርፍ በመወከል የመነሻ ሐሳብ ያቀረቡት ከፍተኛ የህግ ባለሙያውና የዳዲሞስና ፖርትነርስ የህግ ኩባንያ መስራችና ፓርትነር ዶ/ር ዳዲሞስ ሀይሌ እንደተናገሩት በአለም ላይም ሆነ በኢትዮጵያ ያሉ ንግድ ምክር ቤቶችና የተለያዩ የግል ዘርፍ ማህበራት በማስፈጸም አቅም መለያየት ሳቢያ የየራሳቸው ችግሮች እንዳሉባቸው አስረድተዋል ፡፡
ምክር ቤቶችና ማህበራት በዋናነት ሀገራዊና አለም አቀፋዊ የቢዝነስና ኢኮኖሚ ክስተቶችን በቅርበት በማጤን የአባላት ኩባንያዎችን መብትና ጥቅም ለማስከበር በከፍተኛ ደረጃ የመንቀሳቀስ ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶች አሉባቸው ብለዋል፡፡
ተቋማቱ ብቁ፣ ተወዳዳሪ፣ ዘመናዊና አለም ከደረሰበትና ከሀገራት ኢኮኖሚ ዕድገት ፍጥነት ጋር አብሮ ለመራመድ የሚያስችል አስተሳሰብ ይዞ በጋራ መንቀሳቀስ እንዲቻል የንግድ ምክር ቤቶችን አቅም መገንባት ላይ ባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመዋል ።
አዲስ ቻምበር በአቅም ረገድ ከሌሎች አቻ ንግድ ምክርቤቶችም ይሁን የግሉን ዘርፍ መሠረት በማድረግ ከተደራጁ ማህበራት እና ተቋማት አንፃር ብቁ እና የተደራጀ መሆኑን የጠቀሱት ምሁሩ ሌሎችን በመደገፍና የሰፊ አባላቱን የተወዳዳሪነት አቅም ለመገንባት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መረባረብ ይጠበቅበታል ብለዋል።
በቤልጂየም ሐገር ሰፊ የስራ ተሞክሮ ያላቸው ዶ/ር ዳዲሞስ በማብራሪያቸው ንግድን ለመስራት ያሉ ተግዳሮቶችን በየጊዜው ከሚመለከታቸው የፖሊሲ አውጪዎች፣ የመንግስት መስሪያቤቶችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር አብሮ በመስራትና መፍትሄ በጋራ በማፈላለግ የሀገር ውስጥ የንግድ ተዋንያንን በአለም አቀፍ ዘንድ ተወዳዳሪ/competitive/ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል ሲሉ ተደምጠዋል ፡፡
በቢሮ ሐላፊ ደረጃ የአዲስ አበባ ኢንዱስትሪ ቢሮ የአምራች ዘርፍ ሐላፊው አቶ ጳውሎስ ኩሳ በበኩላቸው በሀገሪቱም ሆነ በከተማዋ ላይ የንግድና ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ምህዳርን ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር መንገድ በመጥረግ በኩል የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች ሚናቸው ጉልህ መሆኑን ከአለም ሐገራት ልምድና ተሞክሮ ጋር አያይዘው አቅርበዋል።
እንደ አቶ ጳውሎስ ገለፃ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ ልዩ ትኩረት ማድረግ ተገቢ መሆኑንና የከተማዋ አስተዳደርም አቅጣጫ መሆኑን ተናግረው ዘርፉ አሁንም የፋይናንስና የመስሪያ ቦታን የመሳሰሉ ተግዳሮቶች እንዳሉበት አብራርተዋል ።
በዚህ ረገድ ቢሯቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀራረብ ችግሮቹ እንዲፈቱ ጥረት ማድረጉን ገልፀው አሁንም ካለው ፍላጎት አኳያ ሰፊና የጋራ ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።
አዳዲስ ወጣቶች ሐሳባቸውን ይዘውና ስራ ፈጥረው ወደ ገበያ እንዲገቡ አዲስ ቻምበርን ከመሳሰሉት ተቋማት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ተናግረዋል ።
ሶስተኛው የመድረኩ የመነሻ ፅሁፍ አቅራቢ በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የገበያ ልማት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መከታው አዳፍሬ እንደገለፁት ቢሯቸው አዲስ ቻምበርን ጨምሮ ከሌሎች የንግድ ማህበራት ጋር ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ ተቀራርቦ የንግዱ ማህበረሰብ በምጣኔ ሐብት ውስጥ በቀላሉ ሚናውን እንዲወጣና አመቺ የንግድ አውድ እንዲፈጠር ሰፋፊ ስራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።
በተለይ በፖሊሲዎች፣ ሕጎች፣ ደንቦች እና መመሪያዎች እንዲሁም በልዩ ልዩ ንግድ ነክ ጉዳዮች ላይ የንግዱ ህብረተሰብና መንግስት የሚወያዩባቸውን የግንኙነት መድረኮች መፈጠራቸው ችግሮች ስር ሳይሰዱ ቶሎ የመቀረፍ እድሉን እንዲያገኙ መፍትሄዎቹን ለማፈላለግም ከግልዘርፍ ተቋማት ጋር አብሮ መስራቱ ጠቃሚ መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ አዲስ ቻምበር በአዋጅ የተሠጠውን የንግድና ኢንቨስትመንት ማስፋፋት ስራ በተደራጀ ሁኔታ በከተማዋ እንዲተገብር የከተማዋ ንግድ ቢሮ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ቢሮው ለንግዱ ማህበረሰብ የሚሰጠውን አገልግሎት ቀልጣፋና ከእጅ ንክኪ ውጪ ሆኖ በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ በማድረግ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን አቶ መከታው ጠቁመዋል ።
ይሁን እንጂ አሁንም የንግዱ ማህበረሰብ በየጊዜዉ የሚገጥመውን የአገልግሎትና የመልካም አስተዳደር ተግዳሮቶች ለመፍታት ቢሮው አዲስ ቻምበርን ጨምሮ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ መስራቱን እንደሚቀጥል አስረድተዋል ።
በመድረኩ ላይ በርካታ ጉዳዬች የተነሱ ሲሆን ጠቃሚና በሚመለከታቸው አካላት መፍትሔ የሚሰጣቸው ጉዳዮችን አዲስ ቻምበር አደራጅቶ ክትትል እንደሚያደርግ ለማወቅ ተችሏል ።
