በ 50 ዓመት ትግል ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ለውጦች ቢኖሩም አሁንም ተጠቃሚ ለማድረግ እና ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ቀጣይ ስራዎች እንደሚያስፈልጉ የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አለማቀፍ የሴቶች ቀንን ባከበረበት ወቅት ተጠቁሟል፡፡
በእለቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶች እና ህጻናት ቢሮ ሃላፊ ቆንጅት ደበላ፤ በመከላከያ ሰራዊት የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀነራል ሁሉአገርሸ ድረስ፤የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ዘሃራ መሃመድ፤ የምክር ቤቱ የቦርድ እንዲሁም የማኔጅመንት አባላት፤ የማእከሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ሰልጣኞች፤ የሚዲያ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በነገዋ ሴቶች የተሃድሶ እና ክህሎት ማበልጸግያ ማእከል በመገኘት አክብረዋል፡፡
ምክር ቤቱ ከተለያዩ የልማት አጋሮች ጋር በመተባበር የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ነድፎ በርካታ ሴቶችን በአመራር ፤ በስራ ፈጠራ ክህሎት እና በቢዝነስ ፕላን ዝግጅት ስልጠናዎች በመስጠት ድጋፍ ሲያደርግ የቆየ መሆኑን በንግግራቸው ያነሱት የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ዘሃራ መሃመድ በቢዝነስ ዘርፍ የተሰማሩ ሴት እህቶች ያስመዘገቡትን ስኬቶች እና ያጋጠሟቸው ተግዳሮቶች ምን እንደሚመስሉ የሚያመላክቱ የተሞክሮ መድረክ የሴቶችን ቀን አስመልክቶ ማዘጋጀቱን አንስተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ሴቶች እና ህጻናት ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ቆንጂት ደበላ በበኩላቸውም የከተማ አስተዳሩ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እና ማህበራዊ ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎችን መስራቱን የጠቀሱ ሲሆን በስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ፤ ብድር እንዲያገኙ እንዲሁም የክህሎት ባለቤት መሆን እንዲችሉ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
በእለቱ በ50 ዓመት የሴቶች መብት ተጠቃሚነት ትግል ውስጥ በርካታ ውጤቶች ማግኘት የተቻለ ቢሆንም ዛሬም ህግ የማይፈቅዳቸው ነገር ግን አይነታቸውን እየቀያየሩ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ትኩረት የሚያስፈልጋቸው እና የህግ መሻሻሎች የሚፈልጉ መሆናቸው በእለቱ በቀረበው ጥናት ተጠቁሟል፡፡ በተለይ ሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው እያደገ የመምጣቱን ያህል ደህንነታቸው የተጠበቀ መሆን እንዲችል ሁሉም በባለቤትነት ሊሰራ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
የዚህ መርሀ ግብር አንድ አካል የሆነው የፓናል የውይይት መድረክ የተካሄደ ሲሆን በንግድ ስራ ውስጥ ተሰማርተው ስኬታማ የሆነ ሴቶች የስራና የህይወት ልምዳቸውን ለተተኪ ወጣት ስራ ፈጣሪዎች አካፍለዋል፡፡
በዚህ መድረክ ላይ የምክር ቤቱ ፕረዚደንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድ በማጠቃለያ መልእክታቸው የግል የህይወትና የንግድ ታሪካቸውን ያጋሩ ሲሆን በምንም አይነት መልኩ ወጣቶችና ሴቶች ለምንም አይነት ተግዳሮት እንዳይሸነፉና መብትና ግዴታቸውን በአግባቡ በመወጣት ብልሹ አሰራርን እንዲከላከሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በየአመቱ አለማቀፍ የሴቶች ቀንን በተለያዩ በደማቅ ሁኔታ ያከብራል፡፡
