በአዲስ አበባ የንግድ ፈቃድ የመዝጋት ሂደት እንደ ማውጣቱ ቀላል እንዲሆን ተጠየቀ

ረጅም ጊዜ የቆየው የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ውይይት ተደርጎበት አሰሪ ሆኖ እንዲወጣም የንግዱ ህብረተሰብ ጠይቋል ።

​የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የንግድ ከባቢን ማሻሻልና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ የሚመለከታቸውን የመንግስት አመራሮች እንዲሁም የግሉ ዘርፍ ተዋንያን እና ምሁራንን ያሳተፈ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የጋራ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

​በውይይቱ ላይ ከተነሱት ዋና ዋና ነጥቦች መካከል የንግድ ፈቃድ የማውጣት ሂደት ቢሻሻልም፣ ፈቃድ የመዝጋት አሰራር አሁንም ረጅም ጊዜና እንግልት የሚጠይቅ በመሆኑ እንደ ማውጣቱ ቀላል ሊደረግ እንደሚገባ ተገልጿል።

​በተጨማሪም የሚጣሉ ግብሮች የነጋዴውን አቅም እየተፈታተኑ በመሆናቸው በጥልቅ ጥናት ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑ፣ረጅም ጊዜ የቆየው የንግድ ምክር ቤቶች የማሻሻያ አዋጅ አሰሪ ሆኖ እንዲወጣ፣ በስራ ላይ ላሉ አክሲዬን ማህበራት የካፒታል ገበያ አሰሪና ግልጽ መመሪያ እንዲኖረውና ባንኮች ለጀማሪ አምራቾች ያለ ማስያዣ የሚሰጡትን የብድር መጠን እንዲጨምሩ ጥሪ ቀርቧል።

​በምላሹ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የንግድ ግብይት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ መከታ አዳፍሬ እንደገለጹት፣ የሙያ ብቃት መስፈርቶችን በመቀነስና የኦንላይን አሰራርን በማስፋት የፈቃድ ማውጣት ሂደት እንዲቃለል ተደርጓል።

​ዳይሬክተሩ አክለውም የንግድ ፈቃድ ለመዝጋት ከገቢዎች ቢሮ ክሊራንስ ማቅረብ በቂ መሆኑን ጠቁመው፣ የሚታዩ ክፍተቶችንና የሙስና ችግሮችን ለመቅረፍ ቅንጅታዊ አሰራሮች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አብራርተዋል።

​በሌላ በኩል በከተማዋ የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጳውሎስ ኩሣ፣ በከተማዋ ጫፎች ላይ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ሼዶች በመገንባታቸው እንደ አልባሳት፣ ጫማና የቢሮ ዕቃዎች ያሉ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በስፋት ማምረት መቻሉን ገልጸዋል።

በቤልጂየም ሐገር ሰፊ የስራ ተሞክሮ ያላቸውና የዳዲሞስ እና ፓርትነርስ የህግ ኩባንያ ባለቤት ዶ/ር ዳዲሞስ ሐይሌ በማብራሪያቸው ንግድን ለመስራት ያሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ በየጊዜው ከሚመለከታቸው የፖሊሲ አውጪዎች፣ የመንግስት መስሪያቤቶችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር አብሮ በመስራትና መፍትሄ በጋራ በማፈላለግ የሀገር ውስጥ የንግድ ተዋንያንን በአለም አቀፍ ዘንድ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል ሲሉ ተደምጠዋል።