በአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድ የተመራ የቦርድ እና የማኔጅመንት ቡድን በቃሊቲ የሚገኘውን የነገዋ የሴቶች የተሃድሶና የክህሎት ማበልፀጊያ ማእከልን ጎበኘ ፡፡
ፕሬዚዳንቷ በጉብኝታቸው ወቅት እንደተናገሩት ንግድ ምክር ቤቱ ሴቶችና ወጣት ዜጎች በኢኮኖሚው ውስጥ ተዋናይ እንዲሆኑ፤ ስራ እንዲፈጥሩና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል አበክሮ ይንቀሳቀሳል ብለዋል፡፡ ለዚያም ሲባል ምክር ቤታችን ሴቶች የኢኮኖሚ አቅማቸው በስራ ፈጠራ ረገድ እንዲጎለብትና የንግድ ተወዳዳሪነታቸው እንዲያድግ በርካታ የፕሮጀክት ስራዎንችን የሚሰራ ይሆናል ብለዋል።
የዜጎቻችንን ህይወት ለማሻሻልና የሀገራችንን ችግሮች ለማቃለል እንዲሁም ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በሴቶች አቅም ላይ ትኩረት ያደረገ የእድገት አካሄድ አዋጪና መፍትሄ መሆኑን ጠቁመዋል፡ ፡አዲስ ቻምበርም በማእከሉ እየሰለጠኑ የሚገኙትን ሴቶች ከአባላቱ ጋር በማስተሳሰር የስራ እድል የሚያገኙበትን እድል እንደሚፈጥር ፕሬዚዳንቷ ገልፀዋል ፡ ፡
የማእከሉ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሂርጳሳ ጫላ ለጎብኚዎቹ እንደገለጹት በማእከሉ የተሃድሶ እና የክህሎት ስልጠና የሚያገኙት በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተጋላጭ የሆኑትን ወጣት ሴቶች መሆናቸው ተናግረዋል፡ ፡ማእከሉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተገነባና የሚተዳደር መሆኑንም ተናግረዋል፡ ፡
በማእከሉ ከ 400 በላይ ሴቶች የተሃድሶ እና የክህሎት ስልጠና በመስጠት የስራ እድል እንዲያገኙ ያደርጋል ብለዋል፡ ፡
በከተማው የሚገኙ ባለሀብቶችም የስራ እድል በማመቻቸትም ይሁን በሌሎች መስኮች በአዲስ ቻምበር በኩል ለማእከሉ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡ ፡ማእከሉን የጎበኙት የቦርድ አባላትም በተቻለ አቅም ማእከሉን እና በውስጡ ያሉትን ሴቶች ለመደገፍ ቃል ገብተዋል፡ ፡የምክር ቤቱ ማኔጅመንትም በስራዎቹ ማእከሉን እና ሴቶችን ለመደገፍ ጥረት እንደሚደረግ የምክር ቤቱ ተጠባባቂ ዋና ፀሃፊ አቶ ዘካሪያስ አሰፋ ተናግረዋል፡ ፡
የሴቶች የተሃድሶና የክህሎት ማበልፀጊያ ማእከል በክቡር ጠቅላይ ሚኒሰትር አብይ አህመድ/ ዶ/ር/ እና በከንቲባ አዳነች አቤቤ መጋቢት 5፤2016 ተመርቆ ወደ ስራ የገባ ማእከል ነው፡ ፡ወደ ማእከሉ የሚገቡትን ሴቶች በጤናና ስነልቦና እንዲሁም በክህሎት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡ ፡አዲስ ቻምበር በጉብኝቱ ወቅት የማህበራዊ ሃላፊነቱን ከመወጣት አንፃር ለሴቶች ንጽህና መጠበቂያ የሚውሉ ቁሳቁሶችን አበርክቷል፡ ፡
