በአዲስ ቻምበርና በኤስ ኤ ኬ (S.A.K) በጋራ የሚዘጋጀው 6ኛው የስራ አስፈጻሚዎች መድረክ ተካሄደ

በሁለቱ ተቋማት ትብብር ከአንድ አመት በፊት የተጀመረው የስራ አስፈጻሚዎች መድረክ (Forum for Executive Leadership) ከዚህ ቀደም ስመጥር የኩባያ መሪዎችን፤ስራ አስፈጻሚዎችን የአመራርና የህይወት ልምድ ተሞክሮ በማቅረብ የትውልድ የአመራር ክህሎት ሽግግር እውን እንዲሆን ሚናውን በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡

በተመሳሳይ 6ኛው የስራ አስፈጻሚዎች መድረክ ሀሙስ መጋቢት 25 ቀን 2017 አ.ም በአዲስ አበባ ኢንተር ላግዠሪ ሆቴል የተካሄደ ሲሆን የዚህኛው ዙር መድረክ አምባሳደር ሙሉ ሰለሞንን በእንግድነት አቅርቦ የረጅም አመት የስራና የህይወት ተሞክራቸውን አጋርቷል፡፡

አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን በአማካሪነት፤ በተለያዩ የግል ተቋማት ውስጥ በማናጀርነት፤ በቦርድ አመራር፤ በሰላም አምባሳደርነት፤ በጸሀፊነት ፤ በመምህርነት፤ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ የበጎ ፍቃድ ስራዎችን በመስራት እንዲሁም በተለያዩ የስራ ኃላፊነት ከሰላሳ አመታት በላይ ህዝባቸውንና አገራቸውን ማገልገላቸውን በመድረኩ ላይ ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕረዚደንት በመሆን ፤በፓን አፍሪካን ቻምበር ኦፍ ኮሜርስ በምክትል ሊቀመንበር፤ በአይኤም ኤፍ እና ወርልድ ባንክ ፕሮጀክት ውስጥ ሰርተዋል፡፡

አምባሳደር ሙሉ ሰለሞንን የአመራርና የህይወት ፍልስፍናቸውን ሲያስረዱ መሪነት ጥሩ ተከታይ መሆን፤ ራስን ማብቃት መቻል፤ሁሉንም በእኩል አይን ማየት ነው ብለዋል፡፡

በቻምበር ኦፍ ኮሜርስ  ቆይታቸው ንግድ ምክር ቤቶቹን ከሌሎች ተቋማት ጋር በትብር እንዲሰሩ ሀብት በማፈላለግ ውጤታማ እንደሆኑ የተናገሩት አምባሳደር ሙሉ ለዚህ የጠቀማቸው የተከተሉት የአመራር ጥበብ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

በጀርመንና አካባቢው በአምባሳደርነት የስልጣን ዘመናቸው ኢትዮጵያ በኮቪድ ወቅት የልማት ፈንድ እንድታገኝ፤ ከሌሎች ሀገራት ጋር አጋርነት እንዲፈጠር፤ በትብብር በመስራት የነበራቸውን የአመራር ቁርጠኝነት ተናግረዋል፡፡

የአመራር ጥበብ አድሎአዊ አሰራርን ማስወገድ፤ ችግርን በብልሃት መፍታት፤ አገልጋይነት፤ ለእውነት መቆም፤ አመስጋኝ መሆን፤ ሰራተኛን መረዳትና ማወቅ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ከወላጆቻቸው የስራና የህይወት ክህሎት ልምድን እንደቀሰሙ የሚናገሩት አምባሳደር ሙሉ ወጣቶች ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ፤ የስራ ባህል እንዲያድግ ማድረግ፤ተከባብሮ የመኖር ባህል እንዲዳብር ማድረግ የአንድ መሪ መለያ መሆን አለበት በማለት ለቀጣይ ትውልድ አመራሮች ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡

በሁለቱ ተቋማት ትብብር ከአንድ አመት በፊት የተጀመረው የስራ አስፈጻሚዎች መድረክ (Forum for Executive Leadership) በቀጣይ ሌሎች እንግዶችን ይዞ እንደሚመለስ ለማወቅ ተችሏል፡፡