አዲስ ቻምበርና የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በግሉ ዘርፍ ልማት ዙሪያ በጋራ መስራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መከሩ ፡፡ የአዲስ ቻምበር ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድና የቦርድ አባላቱ ከተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የግዢና የሎጀስቲክስ የጋራ የስራ ቡድን ሊቀመንበር ሚስተር አሊ አሳድ እና ሌሎች አመራሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡
ሚስተር አሊ በውይይታቸው እንደተናገሩት የተባበሩት መንግስታት በሚያወጣቸው የአገልግሎትና የእቃዎች ግዢና ጨረታ የከተማይቱ የንግድ ህብረተሰብ ይበልጥ ተሳታፊ እና ተወዳዳሪ እንዲሆን ከአዲስ ቻምበር ጋር አብረን እንሰራለን ብለዋል ፡፡የንግዱ ሕብረተሰብም ተወዳዳሪ እንዲሆን የአቅም ግንባታ ስራዎች ከአዲስ ቻምበር ጋር በጋራ በመሆን ይከናወናል ብለዋል።
የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድ በበኩላቸው አዲስ ቻምበር በኮሚሽኑም ሆነ በሌሎች የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች የሚወጡ የግዢ ፍላጎቶች መላው የንግዱ ህብረተሰብ ተሳታፊና አቅራቢ የሚሆንበትን ሁኔታ እንፈጥራለን ብለዋል ፡፡ እንዲህ ያሉ የንግድ እድሎችን ለመላዉ የንግዱ ሕብረተሰብ በማቅረብ ተወዳዳሪ እና ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን በግንቦት 15፤2025 በዚህ ጉዳይ በሚያካሄደው የቢዝነስ ኮንፈንስ ላይ አዲስ ቻምበር ስትራቴጂካዊ አጋር እንዲሆንም ጥሪ ቀርቧል፡ ፡ ሁለቱ ተቋማት በቀጣይ በግሉ ዘርፍ እድገት፣ በአቅም ግንባታና የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎችና መሰል የቢዝነስ ልማት ዙሪያ በጋራ ለመስራት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ስር የሚንቀሳቀሱ 29 ተቋማት እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ ። በአዲስ አበባ ብቻ በተለያዩ የንግድ መስኮች የተሰማሩ ከ480 ሺሕ በላይ የንግድ ፈቃድ ያወጡ ነጋዴዎች ይገኛሉ። አዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት እና የተባበሩት መንግስታት የአፍሪቃ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አጋርነት ረዥም አመታትን አስቆጥሯል ።
