በአዲስ ቻምበርና በኤስኤኬ የስልጠና እና አማካሪ ድርጅት በትብብር የሚሰናዳው የስራ አስፈጻሚዎች መድረክ በተሳካ ሁኔታ በአዲስ አበባ ኢሊሊ ሆቴል ተካሂዷል፡፡
ሁለቱ ተቋማት የሚያዘጋጁት ይህ ወሳኝ መድረክ ለስምንተኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን በዚህኛው ዙር በኢትዮጵያ የመድህን ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ ልምድና ተሞክሮ ያካበቱትና በአሁኑ ወቅት የኒያላ ኢንሹራንስ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑትን ዶ/ር ያሬድ ሞላን በእንግድነት አቅርቧል፡፡
ዶ/ር ያሬድ ወደ ሶስት አስርት አመታት ገደማ ከጀማሪ የኢንሹራንስ ባለሙያ እስከ ዋና ስራ አስፈፃሚ ድረስ በማገልገል ለኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ማደግ የበኩላቸውን አስተዋጾ አድርገዋል፡፡
ዶ/ር ያሬድ ኒያላ ኢንሹራንስ ኩባንያን ከመምራት ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ማህበርን እና የአፍሪካ መድህን ሠጪዎች ማህበርን በፕሬዚዳንትነት እያገለገሉ ይገኛሉ ፡፡
Leadership and Service Excellence በሚል መሪ ቃል የተካሄደው የስራ አስፈጻሚዎች መድረክ ላይ የካበተ ልምዳቸውን ያካፈሉት ዶ/ር ያሬድ ሞላ አንድ መሪ ስኬታማ ሊሆን የሚችለው ግልጽ የሆነ ራእይና ግብ ሲኖረው እንዲሁም ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የጋራ ስትራቴጂ በመንደፍ እና ብቃት ያለውን የሰው ኀይል በመመደብ መስራት ሲቻል ነው ብለዋል ፡፡
ከዚህም ባለፈ አንድ መሪ ተቋምን ዘላቂ ለማድረግ ከተፈለገ ከባለ ድርሻ አካላት በተለይም ከደንበኛ ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ሲቻል ነው በሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ዶ/ር ያሬድ ወደፊት የሚያጋጥሙ መልካም እድሎችን ለመጠቀም ሀላፊነት ወስዶ መወሰን እና የሚኖሩ ተግዳሮቶችን ከወዲሁ ለመቅረፍ ስትራቴጂ መንደፍ፤ ከስህተቶች መማር፤ ጽኑ መሆን፤ ራስን የመምራት ክህሎት ማዳበር፤ በየጊዜው ራስን በእውቀት(በንባብ) መገንባት አንድን መሪ ስኬታማ እንደሚያደርገው የረጅም ጊዜ ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡
በኤስኤኬ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር በዶ/ር አደራ አብደላ አወያይነት የተካሄደው 8ኛው ዙር የስራ አስፈጻሚዎች መድረክ በርካታ የኩባንያ አመራሮች የተሳተፉበት ሲሆን እንዲህ አይነት መድረኮች ሀገር በቀል የአመራር እውቀቶችን ተተኪ ወጣት መሪዎች ልምድና እውቀትን የሚቀስሙበት እንዲሁም ዘላቂ የሆኑ ተቋማትን ለመገንባት የሚያስችል ጠቃሚ መድረክ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ የስራ አስፈጻሚዎች መድረክ ላይ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ( አዲስ ቻምበር ) ዋና ፀሐፊ አቶ ዘካሪያስ አሰፋ እንደገለፁት ዶ/ር ያሬድ በኢትዮጵያ የመድህን ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ ያበረከቱት አስተዋጾ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው የሌሎች ተተኪ መሪዎች እና ባለሙያዎች አቅም እንዲገነባ የነበራቸው ሚና እጅግ የሚበረታታ መሆኑን አስረድተዋል ፡፡
ዋና ፀሀፊው አክለውም በአዲስ ቻምበር አነሳሽነት የተጀመሩት የልምድ ልውውጥ መድረኮች በአሁኑ ወቅት የሚስተዋሉ የአመራር ክፍተቶችን ለመሙላት እና ችግሮችን ለመቅረፍ ወሳኝ ሚና አላቸው ብለዋል ፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎች ከዶ/ር ያሬድ ሰፊ ተሞክሮና ልምድ መቅሰማቸውን ከመድረኩ ለመረዳት ተችሏል።
በዚህ መርሐግብር ላይ የተገኙት የቀድሞው የሚድሮክ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈፃሚ እና በአሁኑ ወቅት የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አረጋ ይርዳው እንደገለፁት ይህን ጠቃሚ የስራ መሪዎች መድረክ ወጣቱ በተለይም ወደ ስራ አለም ሊቀላቀሉ የተዘጋጁ ተማሪዎች በስፋት ተሞክሮ የሚወስድበትን መንገድ ተቋማቸው ከአዲስ ቻምበር ጋር በመሆን እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል።
