በ1939ዓም በቻርተር የተቋቋመው የአዲስ አበባ ንግድ ም/ቤት ዛሬ ላይ የ75 አመት አረጋዊ ሆኗል፡፡
75ኛ የምሥረታ በዓሉን ባማረ ሥነስርዓት ለማክበር በአብይ ኮሚቴ አና ሌሎች 16 ንዑሳን ኮሚቴዎች ተቋቁመው ልዩ ልዩ ተግባራትን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የም/ቤቱን ወጥ ታሪክ የሚያወሳ አዲስ መጽሐፍ ማዘጋጀት ይገኝበታል፡፡
መጽሐፉ በገለልተኛ እና ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች የተጻፈ ሲሆን ንግድ ም/ቤቱ በእነዚህ ረጅም አመታት ውስጥ በትውልድ የቅብብሎሽ ሰንሰለት ላይ ያለፈባቸውን መልካም እና ፈታኝ ሁኔታዎችን የሚዘክር ሲሆን የወደፊቱን የጉዞ አቅጣጫ የሚጠቁም ጭምር ነው ተብሏል፡፡
‘የ75 ዓመቱ እንደራሴ፡ የአዲስ ቻምበር ጉዞ’ በሚል ርዕስ በም/ቤቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው ይኸው ወጥ የታሪክ መጽሐፍ ከሃሳብ ጥንስስ ጀምሮ እስከ ዛሬው የም/ቤቱ ተቋማዊ አደረጃጀት እና የወደፊት ራዕይ በተደራጀ መልኩ ዝርዝር መረጃዎችን አካትቷል፡፡
ይኸው መጽሐፍ ለአሁኑ እና ለሚመጣው ትውልድ ስለ ምክር ቤቱ ታሪክ የሚያስረዳ ቋሚ ሠነድ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን በተጨማሪም በአገሪችን የዘመናዊ ንግድ ታሪክ ላይ ጥናት እና ምርምር ለሚያደርጉ ተመራማሪዎች ሁነኛ የመረጃ ምንጭ ሆኖ አንደሚያገለግል ተነግሯል፡፡
መጽሐፉ በውስጥ ይዘቱ ም/ቤቱ ያለፈባቸው ምልካም እና ፈታኝ ሁኔታዎችን የሚዳስሱ፤ የንግዱ ሕብረተሰብ መብት እና ጥቅሞች እንዲከበሩ ስለተደረጉ ጥረቶች፤ እንዲሁም የነጋዴውን እንቅስቀሴ የሚያውኩ የፖሊሲ ሕፀፆች አንጻር የተደረጉ የአድቮከሲ ጥረቶች ይዳስሳል፡፡
የአገራችን የአለማቀፍ ንግድ ግንኙነት እንዲጎለብት መንግስት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን ም/ቤቱ ለአመታት ሲያከናውናቸው የቆየውን የንግድ ማስፋፊያ እና የፕሮሞሽን ሥራዎች በተለይም በውጪ እና በአገር ውስጥ ነጋዴዎች መካከል የንግድ-ለንግድ ውይይት መድረኮች በማዘጋጀት፤ በየአመቱ ዓለማቀፍ የንግድ ትርዒቶችን በማዘጋጀት ያደረገውን አስተዋጽኦ ያስነብባል፡፡
ምክር ቤቱ ለአባላቱ ሲሰጥ ከቆየው አገልግሎቶች መካከል በንግዱ ሕብረተሰብ መካከል በሚፈጠሩ ውዝግቦች ሳቢያ በጋዴዎች ላይ የሚደርሰውን እንግልት፤ተጨማሪ ወጪ እና ጊዜ ለማስቀረት በራሱ የግልግል ዳኝነት ተቋም በኩል የሚያደገውን ድጋፍ ፤የአባላት ልማት ፤ የሥልጠና እና ንግድ ነክ የሆኑ መረጃዎችን በራሱ የሕትመት ውጤቶች አማካኝነት መረጃዎችን ሲያቀርብ መቆየቱን የሚዘክሩ እና ሌሎች ታሪካዊ ክንውኖች ይገኙበታል፡፡
የንግድ ም/ቤቱ የተሳተፈባቸው የማሕበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች ጭምር በዚሁ መጽሐፍ በሥዕላዊ ማስረጀዎች ታጅበው እንደተሰነዱ ተነግሯል፡፡
መጽሐፉ በ19 ምዕራፎች የተከፋፈለ እና 359 ገጾች አሉ::
‘‘ራዕያችን’’ የተሰኘው የም/ቤቱ ሕብረዝማሬ ተሻሽሎ ተዘጋጀ
በ1993 ዓም የተዘጋጀው እና ዘወትር የአዲስ ቻምበር የሬድዮ ፕሮግራም መክፈቻ ሆኖ ሲያገለግል የቆየው እና በሕዝብ ጆሮ የተለመደው ‘ ራዕያችን’ የተሰኘው ዝማሬ መሠረቱን ሳይለቅ በተሻለ የድምጽ ጥራት እና ባማረ ሙዚቃዊ ቅንብር እንደገና ተዘጋጅቶ ወጣ፡፡
የፊተኛው መዝሙር (ጅንግል) በማርሽ ባንድ ታጅቦ የተቀነባበረ ሲሆን ለሬዲዮና ቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች እንዲሁም ለዶክመንተሪዎች በማጀቢያነት እያገለገለ ይገኛል።
አሁን ተሻሽሎ የወጣው ቅጂ የዘማሪዎቹን ድምጽ በጥራት እንዲሰማ ተደርጎ በነፍስወከፍ የሙዚቃ መሣሪያዎች ታጅቦ ለጆሮ እዲስማማ በአማካሪ ባለሙያዎች ( Abiy Arka and etal) እንደተቀናበረ ተነግሯል፡፡
የዚሁ መዝሙር ግጥም ሃሳቡና መልእክቱ ዘመን ተሻጋሪ የሆነ እና ዛሬም ድረስ በግጥሙ ውስጥ የተነሱት ጉዳዮች የቻምበሩ ጉዳዮች እነደሆኑ ለምክርቤቱ የ75ኛ የምሥረታ በአል በተዘጋጀው የታሪክ መጽሐፍ ላይ ተገልጿል።
የመዝሙሩ ስንኞች ሕዝብን ለሥራ የሚያነሳሱ፤ እድገትን የሚሰብኩ፤ስንፍናን የሚኮንኑ፤ ሰርቶ ማግኘትን የሚያወድሱ፤ነጋዴው ለወገኑ ችግር ደራሽ መሆኑን እና ባንዲራ እና ጠንካራ የሀገር ፍቅር ያለው ሕብረተሰብ እንዲሆን የሚያንጹ፤ አገራችን በልጆቿ ሕብረት በልምላሜ እና በሰላም ደምቃ አንድትኖር በሚመኙ በብሩሕ ተስፋ ባዘሉ መልዕክቶች ለትውልድ እንዲያስተላለፉ በጥንቃቄ የተጻፉ እንደሆኑ አዘጋጆች ተናግረዋል፡፡
የግጥሙና የዜማ ደራሲው አቶ ዘገየ ኃይሌ ጀማነህ የተባሉ ሰው አንደሆኑ በመጽሐፉ ተወስቷል፡፡
የም/ቤቱ የሬድዮ ዝግጅት ዘወትር ሐሙስ ከቀኑ 6፡40 – 7፡00 ሰዓት በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ሬዲዮ ጣቢያ በሚያዝያ ወር 1993 ዓ.ም ማስተላለፍ እንደተጀመረ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት ደግሞ በአዲስ ሚዲያ ኔትዎር FM 96.3 በማስተላለፍ ላይ ይገኛል::