የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ከዳኒሽ ኮንፌደሬሽን ጋር በመተባበር ለግብርና አቀናባሪዎች ባዘጋጀው የኩባንያዎች ማሕበራዊ ሃላፊነት አተገባበር ሥልጠና ላይ አንደተገለጸው የንግድ ድርጅቶች የማሕበራዊ ሃላፊነታቸውን በመወጣት ዘላቂ ምርታማነት እና ለትውልድ የሚሸጋገር ድርጅት መፍጠር እንዳለባቸው ተመላክቷል፡፡
በእንግሊዝኛ ምዕጻሩ CSR ወይም የኮርፖሬት ማሕበራዊ ኃላፊት ከቅርብ አመታት ወዲህ በዓለም ዙሪያ እየተለመደ የመጣ የዘመናዊ ንግድ አመራር ዘይቤ እንደ ማለት ነው፡፡ የንግድ ሥራ አንደማንኛውም ሥራ በአካባቢ አና በሕብረተሰብ ላይ የሚያስከትለውን የጎንዮሽ ጉዳት በመቀነስ ንግድን በኃለፊነት መከወን የሚያስችል የንግድ አመራር ዘዴ ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ ትላልቆቹ የዓለም ኩባንያዎች ሳይቀሩ እንደቀደመው ጊዜ አካባቢን እና ሕብረተሰብን በግዴለሽነት እየጎዱ ሳይሆን ከአካባቢና በዙሪያቸው ካለው ሕብረተሰብ ጋር ተስማምቶ ማምረትና በጋራ መጠቀምን እንደ ባሕል ይዘውታል፡፡ ይህም ኩባንያዎቹ በአስተማማኝነት ዘላቂ መሆን ችለዋል ሲሉ ሥልጠናውን የሰጡት አቶ ሳሙኤል ሃይሉ ተናግረዋል፡፡ የማሕበራዊ ሃላፊነትን በአንድ ኩባንያ ውስጥ ለመተግበር የፖሊሲ ሰነድ፤የሠራተኞች ጤንነት እና ደህንነት ፖሊሲ፤ የምርት ጥራት አጠባበቅ፤ እንዲሁም ለአካባቢ እና በዙሪያቸው ካለው ሕብረተሰብ ጋር ያላቸውን ግንኙን ያካተቱ የፖሊሲ ሰነዶች ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ የንግድ ም/ቤቱ የምርምር እና ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል ደንድር በአገራችን ለማሕበራዊ ሃላፊነት ሥራ መልካም ዕድሎች እና ተግዳሮቶች መኖራቸውን የተናገሩ ሲሆን ነገር ግን ፈተናዎችን ወደ መልካም ዕደል በመቀየር ንግድ ም/ቤቱ የንግድ ድርጅቶች ከዘመናዊው የንግድ አመራር ጥበብ አብሮ እንዲሆን የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ከልማት አጋራት ጋር በመተባበር ያከናውናል ብለዋል፡፡