ለሁለት ቀናት የቆየው የአለም ፐብሊክ ሰሚት አፍሪካ 2026 በአዲስ አበባ ተካሄደ፡፡  በዚህ ጉባኤ ላይ አዲስ ቻምበር ከተለያዩ ተቋማት ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን የጋራ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል፡፡

​(ሀምሌ 23 ቀን 2018 አ.ም አዲስ አበባ) የሩሲያ ፌደሬሽን ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያለውን የምጣኔ ሀብት ፤ የቢዝነስ ፤ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመውና በአህጉሩ የመጀመሪያው የሆነው “ወርልድ ፐብሊክ ሰሚት አፍሪካ 2026” (World Public Summit Africa 2026) በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (UNECA) አዳራሽ ተካሂዷል።

አዲሲታ አለም የነቃ አንድነት በሚል መሪ ቃል የተካሄደው “ወርልድ ፐብሊክ ሰሚት አፍሪካ 2026   ከ700 በላይ ተሳታፊዎችን፣ ከ400 በላይ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮችን፣ የሲቪል ማህበራትን፤ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብን እና የመላው አፍሪካ ወጣቶችን በአንድ ላይ ያገናኘ ሁነት ነው።

በጉባኤው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የግሎባል ብላክ ሴንተር  ዋና ጸሐፊ ጸጋዬ ጫማ፣ አዲስ አበባ የአፍሪካ የፖለቲካ መዲና እና የነጻነት፣ የጽናትና የዲፕሎማሲ ተምሳሌት በመሆኗ እንዲህ ዓይነቱን አህጉራዊ ጉባኤ ለማስተናገድ ተገቢዋ ስፍራ መሆኗን ገልጸዋል። አክለውም አፍሪካ በበለጸገ ባህሏ፣ በተፈጥሮ ሀብቷ እና በወጣት ኃይሏ አዲሱን የዓለም ሥርዓት በመቅረጽ ረገድ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን እንዳለባት ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒይ ቴሬክሂን በበኩላቸው ሩሲያ ከአፍሪካ የሲቪል ማህበራት ጋር በትምህርት፣ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ እና በባህል ዘርፎች የጠበቀ ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆኗንም የገለጹ ሲሆን የአፍሪካን መጻኢ እድል የተሻለ ለማድረግ የሲቪል ማህበራት እና የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ ቁልፍ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡

የአዲስ ቻምበር ፕረዚደንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድን በመወከል ንግግር ያደረጉት የምክር ቤቱ ዋና ጸሀፊ አቶ ዘካርያስ አሰፋ ምክር ቤታቸው የንግዱን ማህበረሰብ በመደገፍ ፤ ፈጠራን በማበረታታት እንዲሁም የአገር ኢኮኖሚ እንዲገነባ ጥረት እያደረገ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን ፈጣን የሆነ ንግድና ኢንቨስትመንት እውን እንዲሆን በአፍሪካ አህጉር አስተማማኝ ፖሊሲና ስትራቴጂ እውን መሆን አለበት ብለዋል፡፡

የመክፈቻ ንግግሮችን ተከትሎ የተናጥል የፓናል ውይይቶች የተካሄዱ ሲሆን በባህል፣ በትምህርት፣ በወጣቶች ፤ በኪነ ጥበብ እድገት፤ በቢዝነስና ኢንቨስትመንት ዙርየ ትኩረታቸውን እድርገዋል፡፡

ይህ የአዲስ አበባው ጉባኤ በመስከረም ወር በሞስኮ ለሚካሄደው 2ኛው ዓለም አቀፍ የሕዝብ ሰሚት እና በጥቅምት ወር ለሚደረገው 3ኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ዋና የመነሻ ሀሳቦች የቀረቡበት ሲሆን ጉባኤው መቀመጫውን ሞስኮ ካደረገው “ወርልድ ፒፕልስ አሴምብሊ” በተጨማሪ ከግሎባል ሰርቭ እና ከግሎባል ብላክ ሴንተር ጋር በትብብር የተዘጋጀ ነው።

የ”ወርልድ ፐብሊክ ሰሚት አፍሪካ 2026″ ተባባሪ የሆነው አዲስ ቻምበር ከአለም አቀፉ የህዝቦች ጉባኤ፣ ከሩሲያው ክራስኖዳር ንግድ ምክር ቤትና ከተለያዩ የሩሲያ የንግድና የኢኮኖሚ ተቋማት ጋር አብሮ ለመስራት በሚያስችለው ጉዳዮች ዙሪያ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።
የመግባቢያ ስምምነቱን የፈረሙት የአዲስ ቻምበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ዘሐራ መሐመድ ናቸው።

አዲስ ቻምበርየግሉ ዘርፍ ድምጽ!