አዲስ ቻምበር በአካባቢያዊ፣ ማህበራዊና መልካም አስተዳደር/ESG/ ዙሪያ ለአባላቱ ስልጠና ሰጥቷል ፡ ፤
(መስከረም 8; 2018) ሰዎች በየዕለቱ በሚያደርጉት ማንኛውም እንቅስቃሴ በአካባቢያቸውና በዙሪያቸው በሚኖር ሕ/ሰብ ላይ የተለያዩ ተጽዕኖ ማድረጋቸው አይቀርም፡፡
እነዚሀ ጉዳቶችን ለመታደግ በተለይ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ቢዝነሳቸውን በኃላፊነት መንፈስ እንዲከውኑ የሚያስችላቸው በእንግሊዝኛ ምዕጻር ESG –Environment Social and Governance/ አልያም RBC-Responsible Business Conduct/ መርሆች መተግበር ከቅርብ አመታት ወዲህ እየተለመደ መጥቷል፡፡
ዛሬ ላይ የዓለም የንግድ ሥርዓት ላይ አንድ ላኪ ድርጅት ማሟላት የሚገባው አንዱ ግዴታ እይሆነ መጥቷል፡፡
አዲስ ቻምበር ይህንን ወቅታዊ ርዕሰ ጉዳይ ለአባላቱ ስልጠናና እና መረጃዎች ሲያደርስ ቆይቷል፡፡
ምክር ቤቱ ዛሬም በግብርና፤ በአልባሳት፤ በቱሪዝም፤ በፍራፍሬ እና በምግብ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ አባል ኩባንያዎች በተዘጋጀው ሥልጠና ላይ ለላኪ አባል ድርጅቶች የአካባቢያዊ እና ማህበራዊ አስተዳደር/ ESG/RBC/ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው የዘርፉ ተመራማሪ የሆኑት ቃልኪዳን ኢሳያስ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ESG/RBC ምርታማነት ያሳድጋል፤ወጪን ይቀንሳል፤ለኩባንያዎች መልካም ስምና ዝና እንዲያተርፉ ያስችላል፡፡
በተጨማሪም ከባንኮች ብድር ለማግኘት እንዲሁም በዓለም ገበያ ላይ ብቁ ተወዳዳሪ ለመሆን ያስችላል ሲሉ ዶ/ር ቃልኪዳን አብራርተዋል፡፡
በተለይ የሀገራችን ባንኮች ዛሬ ላይ ለብድር ጥያቄዎች ቅድሚያ የሚሰጡት ለአረንጓዴ ኢንቨስትመንት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ስለዚህ ጀማሪ፤አነስተኛ፤መካከለኛ እንዲሁም ትላልቅ ቢዝነሶች ከወዲሁ በአካባቢ፤በማሕበራዊ እና በሠራተኞች አያያዝ ላይ ሃላፊነታቸውን የሚወጡበትን ESG/RBC ፖሊሲ አዘጋጅተው ከወዲሁ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
በዘመናዊው የንግድ አስተምህሮ አንድ የንግድ ተቋም ለስኬት ከሚያበቁት አንኳር ቅድመ ሁኔታዎች መካከል የሰራተኞችን ክህሎት ማሳደግ፤ ደህንነታቸውንና ጥቅማቸውን ማክበር፤ የሥራ አካባቢን የብክለት መከላከያ ዘዴዎችን መጠቀም፤ በሕብረተሰብ ልማት ሥራዎች ላይ ተሳትፎ ማድረግ እንዲሁም ከአካባቢ ጋር ስምም ሆኖ ማምረት ሲችል ነው የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ለአንድ በእርሻ ዘርፍ ለተሰማራ የቢዝነስ ድርጅት ESG/RBC ፖሊሲን ለመተግበር ከሕገወጥ የአቅርቦት ሰንሰለቶች የጸዳ፤ ትናንንሽ ገበሬዎች መደገፍ፤ ምርቱን ከባዕድ ነገሮች ጠብቆ እና ለደንበኞቹ ታማኝ መሆን አለበት ፡፡
የንግድ ሥራ ብዙ ዘርፎች ያሉትና በባሕሪያቸው በጣም የተለያዩ ሲሆኑ የሚያደርሱት ተጽእኖም በመጠንም በአይነትም የተለያዩ ናቸው፡፡
አንዴት ESG/RBC ፖሊሲ መቅረጽ አንደሚቻል ከተሳታፊዎች ለቀረበው ጥያቄ፤ ለሁሉም የቢዝነስ ዘርፎች ወጥ የሆኑ የESG/RBC መርሆች አለመኖራቸውን አሰልጣኝዋ ተናግረዋል፡፡
አንድ አምራች ወይም አገልግሎት ሰጪ ድርጅት በቅድሚያ የአቅርቦት ሥርዓቱን በሚገባ መፈተሸ አለበት፡፡
እንደ ድርጅቱ አፈጣጠርና እንደ ተሰማራበት ዘርፍ ፤በሰውና በእንስሳት እና በአካባቢ ላይ ስለሚያስከትለው ጉዳት አስቀድሞ ማጥናት አለበት፡፡
ተሳታፊዎች የESG/RBC መርሆዎችን ከድርጅታቸው ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር አዛምደው በሚተገብሩበት ዘዴዎች ላይ የቡድን ውይይትና የልምድ ልውውጥ አድርገዋል፡፡
ከስልጠናው ባገኙት ግንዛቤ መሠረት ሰልጣኞች የESG/RBC መርሆዎችን ተግባራዊ በማድረግ የሥራ አካባቢያቸውን አየር፤ውሃ፤እንስሳት እና የሰዎች ደህንነት ጠብቀው ለማምረት በየድርጅታቸው ዝግጅት አንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
ስልጠናው በአዲስ ቻምበር እና በዴኒሽ ኢንዱስትሪ ትብብር የተዘጋጀ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
