በመንግስትና በንግዱ ሕብረተሰብ መካከል ያለው ግንኙነት ይበልጥ ሊጠናከር ይገባል

በመንግስትና በንግዱ ሕብረተሰብ መካከል ያለው ግንኙነት ይበልጥ ሊጠናከር ይገባል
ወ/ሮ መሠንበት ሸንቁጥ የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማሕበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት

በይድነቃቸው ዓለማየሁ
ጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በተጠራው የምክር ቤቱ 14ተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ለዳይሬክተሮች ቦርድ በፕሬዝዳንትነት የተወዳደሩት ወ/ሮ መሠንበት ሸንቁጥ አሸናፊነታቸው ከታወቀ በኋላ ባደረጉት ንግግር መንግስት ለንግዱ ህብረተሰብ ያለውን ትኩረት እንዲያሳድግና በዘላቂነት በጋራ እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአዲሱ ቦርድ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን አስመልክቶም ወ/ሮ መሠንበት ሸንቁጥ ሲያብራሩ፣ የንግዱን ሕበረተሰብ ጥያቄዎች እና ፍላጎቶችን በማንሳት ለመንግሥት ማቅረብ እና መንግሥትም ለጉዳዮቹ ትኩረት ሰጥቶ እና አስፈላጊውን ማሻሻያዎችን ተግባራዊ እዲያደርግ በትጋት እንሠራለን ብለዋል፡፡
ታክስ፤የፋይናንስ አቅርቦት እና የመሳሰሉት አንኳር የነጋዴው ጥያቄዎችን ቅድሚያ በመስጠት ምላሽ እንዲያገኙ ተከታታይ ውይይቶችን ከመንግስት ጋር ለማካሄድ ጥረት እናደርጋለን ያሉት አዲሷ ፕሬዚዳንት ፣ በሰለጠነው ዓለም ሸማቹ የሕብረተሰብ ክፍል ለንግድ ምክር ቤት አባላት ያለው ክብር እና ፍቅር በእኛም አገር ይኸው ባሕል እንዲፈጠር ከቦርድ አባላት እና ከመላው የንግዱ ሕብረተሰብ ጋር በጋራ ጥረት እናደርጋለን ብለዋል፡፡
የአዲሱ ተመራጭ ቦርድ አባላት በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ላይ ሰፊ ልምድ እና ዕውቀት ያካበቱ ሲሁኑ ከቀድሞዎቹ ተጨማሪ ልምድን በመቅሰም የነጋዴውን ድምጽ በመንግሥት በኩል ትኩረት እንዲያገኝ የአጭር፤የመካከለኛ እና የረዥም ጊዜ እቅድ በጋራ አዘጋጅተን እንሰራለን ፤ ለዚህም መላው የንግድ ሕብረተሰብ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡